‹‹የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም ሆነ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ችግሩም መፍትሔውም ከታች መምጣት ይገባዋል›› ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ

ቤኔፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE ) ፕሮግራም በደራሼ፣ ቁጫ፣ ም/አባያና ዛላ ወረዳዎች ያከናወነውን የዳሳሳ ጥናት አስመልክቶ የማኅበረሰብ ተሳትፏዊ ጥናት ግኝት ወርክ ሾፕ ከታኅሣሥ 9-10/2011 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ በወርክ ሾፑ የጉዳዩ ተቀዳሚ ባለቤት የሆኑት አርሶ አደሮች፣ የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የጤና ባለሙያች እና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ ፕሮጀክቱ ከሰኔ 2010 ዓ/ም ጀምሮ ይፋ መሆኑንና በኔዜርላንድስ መንግሥት እንደሚደገፍ ተናግረው በዋናነት ውጤታማ ተሞክሮዎችን በማላመድ፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማዳረስ፣ በየወረዳውና በየቀበሌው በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማትን አቅም በመገንባት እንዲሁም የፈጠራ ሥራዎችን በማከናወን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ይሠራል ብለዋል፡፡

እንደ አስተባባሪው ገለፃ ፕሮጀክቱ ወደ ተግባራዊ ሥራ ከመግባቱ በፊት ችግሮችን ቀድሞ መለየት አስፈላጊ በመሆኑ በአራቱ ወረዳዎች በሚገኙ 8 ቀበሌዎች ህብረተሰቡን ያሳተፈ የዳሰሳ ጥናት ለሁለት ወራት ተደርጓል፡፡ ችግሮችም ሆኑ መፍትሔዎች ከላይ ወደ ታች ሳይሆን ከታች ወደ ላይ ሲመጡ በተሻለ ደረጃ ውጤት ላይ መድረስ ይቻላል ያሉት ዶ/ር መብራቱ ይህም ወርክ ሾፕ በዳሰሳ ጥናቱ የተለዩ ችግሮችን ትክክለኛነት በአርሶ አደሮችና በአርሶ አደሩ ዙሪያ በሚሠሩ ባለሙያዎች ለማስገምገም እንደተዘጋጀ ገልፀዋል፡፡

በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የገጠር ልማትና ግብርና ኤክስቴንሽን መምህርና የዳሰሳ ጥናቱ ተሳታፊ  መ/ር አግደው አበበ አሥር መለያ ዘዴዎችን በመጠቀም ችግሮችን መለየት መቻላቸውን ገልፀው ፕሮጀክቱ  በዚህ መልኩ ሥራውን በጥናት መጀመሩ ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ ያግዛል ብለዋል፡፡

ህብረተሰባችን የምግብ ዋስትና ችግር ያለበት መሆኑ ይታወቃል ያሉት የቁጫ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቲቆ ትላንቴ በሁለት ቀናት የወርክ ሾፑ ቆይታቸው በመስኩ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመለየት የነበራቸውን ግንዛቤ ማዳበራቸውን ገልፀዋል፡፡ ኃላፊው ከዚህ በኋላ ከቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮጀክትም ሆነ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ከግቡ ለመድረስ በቁርጠኝነት ልንሠራ ያገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ አገራችን ኢትዮጵያ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰልፍ በምታደርገው ጥረት ውስጥ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ  አብይ ጉዳይ በመሆኑ ለስኬቱ እንደ ቤኔፊት ሪያላይዝ ያሉ ፕሮግራሞች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ገልፀዋል፡፡ የቀርቡት የዳሰሳ ጥናት ሰነዶች በውይይት በልጽገው አገራዊ ፋይዳ ሊኖራቸው ይገባልም ብለዋል፡፡