በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የትምህርት ዘርፍ አማካሪ ዳይሬክቶሬት ለዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ተማሪዎች በውጪ አገር የትምህርት ዕድል አሰጣጥ፣ የቪዛ ሂደት፣ የመምህራን ልምድ ልውውጥ፣ በውጪ አገር ተቋማት የሥራ እድል ማመቻቸት እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የልምድ ልውውጥ የውይይት መድረክ ከታኅሣሥ 12-13/2011 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

 

ፕሮግራሙ በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የህዝብ አስተዳደር ጉዳይ ክፍል ሥር የትምህርት ማማከር አገልግሎት ማዕከል በኩል ተማሪዎች በተለያዩ የዓለም አገራት ዕውቅና ባላቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተአማኒ፣ ሁሉን አቀፍ እና ወቅታዊ መረጃ ባለው መልኩ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ እገዛ ያደርጋል፡፡

በነፃ የትምህርት ዕድል፣ በፓርትነርሽፕና በማማከር አገልግሎት በቂ መረጃና እገዛ ለመስጠት የተቋቋመው ማዕከል በአብዛኛው አገልግሎቱ በአዲስ አበባ ብቻ ተገድቦ የነበረ ሲሆን በሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆን ሀሳብ በመለዋወጥና በማገዝ የዕድሉ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለማስፋት በማለም መድረኩ መዘጋጀቱን በኤምባሲው የትምህርት ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ ተክለሚካኤል ተፈራ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያና አሜሪካ በተለያዩ ዘርፎች ለረጅም ጊዜ የጠበቀ ግንኙነት ያላቸውና የበርካታ ታሪክ ባለቤት መሆናቸውንም አውስተዋል፡፡

ለነፃ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል መሠረታዊ በሆኑት የትምህርት ምርጫዎች ፍላጎት ጥናት፣ የፋይናንስ አግባብ ጥናት፣ የማመልከቻ አቀራረብ፣ የማመልከቻ ምሉዕነት እንዲሁም የጉዞ ቅድመ ሁኔታን በተመለከተ አቶ ተክለሚካኤል ዝርዝር ነጥቦችን አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም ለመምህራን በተለያዩ የውጪ አገር ተቋማት የሥራ ፍለጋ፣ የመምህራንና ተማሪዎች ልውውጥ (staff exchange) እንዲሁም ለተማሪዎች የተለያዩ የስኮላርሽፕ አማራጮችን ማመቻቸት፣ የስኮላርሽፕ ማመልከቻና የቪዛ ሂደትን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት አቅርበው በባለሙያው ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ትምህርት አገሪቱ ካለችበት የድህነት አዘቅት መውጫ ብቸኛ መንገድ መሆኑን የተናገሩት የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ግምገማና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ንጉሴ ታደገ ለዚህም እንደ አሜሪካ ባሉ በትምህርት ዘርፍ የተሻለ አቅም ባካበቱ አገራት ጥራት ያለው ትምህርትና ስልጠና ማግኘት ለለውጡ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡

በአሜሪካ አገር 475 ዕውቅና ያላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በ175 የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ሲሆን በ2010 ዓ/ም በአሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነፃ ትምህርት ዕድል ካገኙ አንድ ሚሊየን ተማሪዎች መካከል ከ1800 የሚልቁት ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የዕድሉ ተጠቃሚ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ200 ብልጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፣ መምህራን እና ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡