የተማሪዎች ኅብረት የ2011 ዓ.ም የ3 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀረበ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅብረት የ2011 ዓ.ም የ3 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ታኅሣሥ 21/2011 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በተገኙበት አቅርቧል፡፡የተማሪዎች ኅብረት ዓላማ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን በተለይም በመማር ማስተማር፣ በመልካም አስተዳደር፣ በአገልግሎት ሰጪና ተቀባይ መካከል ያሉ ክፍተቶችን መቅረፍ ነው፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ቃልኪዳን አባይነህ እንዳብራራችው በ2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የኅብረቱን አባላት በማስተባበር ለነባር እና አዲስ ገቢ ተማሪዎች አቀባበል ማድረግ፣ ከSAM UP ክበብ ጋር በመሆን ለአዲስ ተማሪዎች ቲቶሪያል መስጠት እንዲሁም የዕለት ተዕለት አገልግሎት፣ የመዝናኛ እና የመማር ማስተማር ሥራዎችን መደገፍ፣ በሁሉም ካምፓሶች ነባር ተማሪዎች እንደገቡ የመማክርት የማሟያ ምርጫ እና የኮሚቴ ምልመላ ማድረግ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተጨማሪም ተማሪዎች ከአልባሌ ድርጊት እንዲጠበቁ ከማድረግ አንፃር ከደኅንነት አካላትና ከሰላም ፎረም ጋር በመሆን መቆጣጠር፣ ከምግብ ቤት አገልግሎት ጋር በመተባበርና ከሠራተኞች ጋር ውይይት በማድረግ በምግብ ቤት ዙሪያ ያሉትን ክፍተቶች መሙላት፣ በሁሉም ካምፓሶች የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንዲሁም ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የማደሪያ እና የመማሪያ አካባቢ ምቹ የማድረግ ሥራም ተከናውኗል፡፡

በመማሪያ ክፍልና በቤተ-መጽሐፍት የወንበር እጥረት፣ የተግባር ትምህርት መዳከም፣ የሴክሽን ተጠሪ መምህራን በታቀደው መጠን አለመሥራት፣ የሴቶች የማጠናከሪያ ትምህርት አለመጀመር፣ በምዝገባ ጊዜ የSMIS ኔትወርክ መቋረጥ) እና የ Wi-fi አገልግሎት በቂ አለመሆን በሩብ ዓመቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

በተጨማሪም በጫሞ ካምፓስ የምግብ አቅርቦት ጥራት ችግር፣ በሳውላ ካምፓስ የምክር አገልግሎት ቢሮና የመጠጥ ውኃ ችግር አለመቀረፍ በሁሉም ካምፓሶች ደኅንነት ችግር መኖር፣ በሳውላ ካምፓስ የመፀዳጃ ቤት እጥረት እንዲሁም የውኃ ታንከሮች አለመታጠብ ችግሮችና የመሳሰሉት በውይይቱ ወቅት ተነስተዋል፡፡