ዩኒቨርሲቲው በአርባ ምንጭ ከተማ የጽዳት ዘመቻ አካሄደ

ዩኒቨርሲቲው ‹‹አንድ ቅዳሜን ለሕዝቤ! ኑ ከተማችንን አብረን እናፅዳ፣እናልማ፣ ውብም እናድርጋት!›› በሚል መሪ ቃል በአርባ ምንጭ ከተማ ታኅሣሥ 20/2011 ዓ.ም የበጎ አድራጎት የጽዳት ዘመቻ አካሂዷል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የጽዳት ዘመቻውን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት የአርባ ምንጭ ከተማ የዩኒቨርሲቲው መገኛ ከተማ በመሆንዋ ከተማዋን ውብ፣ የለማችና ፅዱ ማድረግ ለከተማው ሕዝብም ሆነ ለዩኒቨርሲቲው ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ የበጎ አድራጎት ጽዳት ዘመቻውን ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ከጥናት፣ ትምህርትና ከትርፍ ጊዜያቸው በመቀነስ መሳተፋቸው የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ከጽዳት ዘመቻው በተጨማሪ ከተማዋን አረንጓዴ ለማድረግ የችግኝ ተከላና ሌሎችም ተግባራት የሚከናወኑ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝደንቱ የከተማው ማኅበረሰብና አመራሩ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ከተማ ደ/ኢ/ህ/ዴ/ን/ን/ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበራ አባይነህ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ያስጀመረው የበጎ አድራጎት ሥራ እገዛው የጎላ ሲሆን በቀጣይ የከተማውን ነዋሪ በሙሉ በማሳተፍ የከተማ ጽዳት እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ያሳየው ተሞክሮ ከተማ አስተዳደሩንም ሆነ ነዋሪውን በጣም ያነቃቃ ተግባር በመሆኑ ሊመሰገን ይገባልም ብለዋል፡፡
በጽዳት ዘመቻው የተሳተፉ የከተማው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በበጎ አድራጎት ሥራው ላይ በመሳተፋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ዘመቻው እንዳነቃቃቸውና አካባቢያቸውን ለማጽዳትና ለማልማት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የጽዳት ዘመቻው መነሻውን ከጋሞ አደባባይ አድርጎ ወደ አምስቱ ካምፓሶች የተከናወነ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና ተማሪዎች እንዲሁም የከተማው አመራሮችና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡