የዩኒቨርሲቲው የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ

የዩኒቨርሲቲው የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ የካውንስል አባላት በተገኙበት ጥር 10/2011 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡
የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝ/ት/ግ/ዳይ/ዳይሬክተር አቶ ገዝሙ ቀልቦ ባቀረቡት የ6 ወራት የሥራ ክንውን ሪፖርት እንደተመለከተው ከዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሠራተኞች፣ ከተማሪ ተወካዮች፣ ከከተማው አስተዳደርና ከዞኑ መንግሥት እንዲሁም ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ጋር በጋራ በመስራት የመማር ማስተማር ሂደት ሠላማዊ እንዲሆን መደረጉ፣  አዲስ ለተቀጠሩ መምህራን በማስተማር ክህሎት፣ በሙያ ሥነ-ምግባርና በሌሎች ሙያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና መሰጠቱ፣ የትምህርት አግባብነትና ጥራት ለማሳደግ ኮርሶች ሙሉ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

በሙሉ በሞጁላር ሥርዓተ-ትምህርት ዘዴ እየተሰጡ መሆኑ፣ ለአካል ጉዳተኛ፣ ከታዳጊ ክልሎች ለመጡና ለሴት ተማሪዎች ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑ፣ በቂ የተግባቦት ሥራ በሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም በድህረ-ገፅና በማህበራዊ ሚዲያ መከናወኑ፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ለማነቃቃት በከተማው የፅዳት ዘመቻ መካሄዱ፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ማኅበረሰብ ታዋቂ እንግዶችን በመጋበዝ የማነቃቂያ ንግግሮች መደረጋቸው፣ የAMU-BENEFIT REALISE ፕሮጀክት ከኔዘርላንድ አገር መንግስት ጋር በመተባበር የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በአካባቢው አራት ወረዳዎች ሥራ መጀመሩና የዳሳሳ ጥናት ተደርጎ የዘርፉ ባለድርሻዎች የተገኙበት ወርክሾፕ መካሄዱ በግማሽ ዓመቱ ከተመዘገቡ አበይት ስኬቶች መካከል ናቸው፡፡

በተጨማሪም የነፃ ህግ አገልግሎት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉ፣ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት በዘጠኝ መዕከላት እየተሰጠ መሆኑ፣ በሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት አማካይነት ሶስት ት/ቤቶች የሶላር ኤሌትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው፣ በአካባቢው ከሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ልዩ ወረዳዎች ለሚሰሩ 70 የመንግስት ሠራተኞች እንዲሁም ከሕክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ጋር በተግባር ትምህርት አብረው በሚሠሩ ሆስፒታሎች ለሚሰሩ 17 የጤና ባለሙያች ነፃ የትምህርት ዕድል መሰጠቱ፣ ነፃ የቀዶ ጥገና ህክምና አገልግሎት በአርባ ምንጭና ገረሴ ሆስፒታል ለሚገኙ ታካሚዎች መሰጠቱ  ከስኬታማ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸው አቶ ገዝሙ ቀልቦ ባቀረቡት ሪፖርት ተመልክቷል፡፡
በዩነቨርሲቲው በርካታ ተሽከርካሪዎች ያረጁ በመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ የተሸከርካሪ እጥረት መኖሩ፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር ወቅታዊ የበጀት ፍሰት አለመኖር፣ የአስተዳደር ሠራተኞች የJEG ምደባ አለመጠናቀቅና ተቋሙ በ2011 የተቀበላቸው አዲስ ተማሪዎች ብዛት ከዕቅድ በላይ በመሆኑ የተማሪ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጫና መፍጠሩ በግማሽ ዓመቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ደካማ አፈጻጻሞች መሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንዳሳሰቡት ሠላማዊ መማር ማስተማር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከተማሪ አደረጃጀቶች፣ ከአከባቢው መስተዳደርና ሕብረተሰብ ጋር ያለውን ትስስር ማስቀጠል፣ በትምህርት ጥራትና መልካም አስተዳደር ፎረም ውይይቶች ክፍተቶችን በማስተካከል መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ጠንክሮ መሥራት፣ አዲስ የተፈጠሩና የተላመዱ የምርምር ውጤቶችና ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተጠቃሚው ማህበረሰብ የማሸጋገር ሥራ አጠናክሮ መሥራት፣ ነባር የግንባታ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ እንዲጠናቀቁ እንዲሁም  አዲስ ለተጀመሩ ግንባታዎች  በቂ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፣ በግማሽ ዓመቱ  ዕቅድ  አፈጻጸም ዝቅተኛ ውጤት የተመዘገበባቸውና ያልተሰሩ ተግባራትም  በቀጣዩ ግማሽ ዓመት አፈፃፀም  ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊከናወኑ ይገባል፡፡
በመድረኩ ላይ ሪፖርቱን መሠረት የደረጉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው በየዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት