አዲስ ለተቀጠሩ የፎረንሲክ ኬምስትሪና ቶክሲኮሎጂ መምህራንና የቤተ-ሙከራ ባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠ

የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ በፎረንሲክ ኬምስትሪና ቶክሲኮሎጂ ት/ክፍል በ2011 ዓ.ም አዲስ ለተቀጠሩ መምህራን፣
የቤተ-ሙከራ ባለሙያዎች እና ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽ/ቤት ለመጡ ፖሊስ አባላት  <<VSC-8000 Document Analyzer>> የተሰኘ የሰነድ ምርመራ ማሽን አጠቃቀም መሰረታዊ ጽንሰ ሃሳብና የተግባር ልምምድ ስልጠና  ከታህሳሥ 22-24/2011 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፎረንሲክ ዳይሬክቶሬት የሰነድ ምርመራ  ባለሙያ የሆኑት አቶ ይርጋለም ፋንታ እንደገለጹት ስልጠናው በአገራችን  እየተስፋፋ  ያለውን  ወንጀልና ወንጀል ነክ ጉዳዮችን ለመከላከልና በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ማፍራት  ሲሆን ተሳታፊዎች ስለሰነድ ምርመራ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የተማሩትን ትምህርትና ያገኙትን ዕውቀት በተጨባጭ መሣሪያ በተግባር ተለማምደው በሚሰሩበት ወቅት ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግና የሚያጋጥማቸውን  ችግር በቀላሉ እንዲፈቱ ለማስቻል ነው፡፡
የፎረንሲክ የሰነድ ምርመራ መሣሪያ የተጭበረበሩ ዶክመንቶችን፣ የብር ኖቶችን፣ ፓስፖርቶችን፣ የእጅ ፅሁፍ አሻራዎችን ፣ ቀለማትንና ያረጁ ወረቀቶች ላይ ያሉ ፅሁፎችን፣ ፊርማና ማህተም ትክክለኛነት ለመለየት ያስችላል ያሉት በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፎረንሲክ ዳይሬክቶሬት የሰነድ ምርመራ ባለሙያ ወ/ሮ ሰዓዳ አብደላ ከዚህ በፊት ለፎረንሲክ ሳይንስ ብዙ ትኩረት ያልተሰጠ በመሆኑ በአገሪቱ  ያልተስፋፋ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በቀጣይነት ለሚመለከታቸው የዘርፉ ባለሙያዎች በመስጠት አቅም ለማጎልበት በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡
ተሳታፊ ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ገንቢ፣ ወቅታዊና አሳታፊ ከመሆኑም በላይ በተግባር የተደገፈና በሚሰሩበት ዘርፍ የነበራቸውን ክፍተት የሚሞላና የሚገጥማቸውን ችግር በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል መሆኑን ተናግረው ያገኙትን ግንዛቤ፣ ልምድና ዕውቀት ለተማሪዎችና ለሌሎች ባለሙያዎች በማካፈል የጋ ግንዛቤ ለመፍጠር ቃል ገብተዋል፡፡
በስልጠናው አዲስ የተቀጠሩ የፎረንሲክ ኬምስትሪና ቶክሲኮሎጂ  መምህራን፣ የፎረንሲክ ቤተ-ሙከራ ባለሙያዎችና ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽ/ቤት የመጡ የፖሊስ አባላት ተሳትፈዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት