ዩኒቨርሲቲው በ2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ሴሚስተር የመማር ማስተማር ሥራ ማጠቃለያና የፈተና ዝግጅት ዙሪያ ውይይት አካሄደ

ዩኒቨርሲቲው ከሁሉም ኮሌጆችና ኢንስቲትዩቶች ከተወጣጡ የፋካልቲ ኃላፊዎች፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ ዲኖች፣ ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍል ዳይሬክተሮችና ም/ፕሬዝደንቶች ጋር በ2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ሴሚስተር የመማር ማስተማር ሥራ ማጠቃለያና የፈተና ዝግጅት፣ አስተዳደር፣ እርማትና ውጤት አሰጣጥ ዙሪያ ጥር 2/2011 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል፡፡ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የመ/ር ቁልፍ ተግባራት ማቀድ፣ ማስተማርና መገምገም ሲሆን ተከታታይ ምዘና ዋና ዓላማው ተማሪውን ለማብቃት ስለሆነ የፈተና አሰጣጥ ሂደታችንን በየጊዜው ማሻሻል ይጠበቅብናል ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ የፈተናውን ተኣማኒነትና ትክክለኛነት መጠበቅ ይኖርብናል ብለዋል፡፡ የፈተና ጥያቄዎችን ከትምህርቱ ቁልፍ ዓላማዎችና በማስተማር ወቅት ትኩረት ከተሰጣቸው ይዘቶች  ጋር ማጣጣም፣ የመፈተኛ ክፍል ስፋት፣ ብርሃን፣ መቀመጫና ጠረጴዛ  ከተፈታኞች ብዛት አንጻር በቂ መሆኑን ማረጋገጥ እንዲሁም አቀማመጡን ለኩረጃ የማይመች ማድረግና የፈተና አዳራሽን ከአካባቢው ከሚረብሹ ድምጾች ነፃ ማድረግ እንደሚገባ ፕሬዝደንቱ ተናግረው ከማንኛውም አድልዎ በራቀ ሁኔታ የፈተናውን እርማት በማካሄድ ውጤት ማሳየትና ቅሬታ ካለ መርምሮ ተገቢ ምላሽ መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም የመጀመሪያ አጋማሽ የመማር ማስተማር ሥራ አጀማመር፣ የክፍለ ጊዜ አሸፋፈን፣ የባከነና የተካካሰ ክፍለ ጊዜ፣ ለሴቶችና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የተደረገ ድጋፍ፣ ተከታታይ ምዘና ያለበት ደረጃ እንዲሁም የትምህርት ፕሮግራሞች አከፋፈትና ግምገማ በዝርዝር ያብራሩት የተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይ/ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማሪያም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ሲቀሩ 2ኛ ዓመትና ከዚያ በላይ የደረሱ ተማሪዎች በታቀደው ጊዜ ትምህርት መጀመራቸውን፣ ለሴቶችና ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የሚሰጡ ድጋፎች በወቅቱ አለመጀመራቸውን፣ የጀመሩ መምህራንም ቢሆኑ በቂ ሰዓት ለማስተማር ያለመቻላቸውንና እንዲሁም ተከታታይ ምዘናም ወቅታዊ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት  ውይይቱ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና ያለው ሲሆን  በዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ካላንደር መሰረት የመማር ማስተማር ሥራቸውንና የሚጠበቅባቸውን ኃላፍነት በአግባቡ ለመወጣት ተግተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት