በእሴት ሰንሰለት ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ

የዩኒቨርሲቲው እንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት በዩኒቨርሲቲው አምራች እንደስትሪና ቴክኒክና ሙያ ክላስተር ቴክኖሎጂ ትስስር ውስጥ ከሚገኙ ኮሌጆችና የዘርፉ ተቋማት ለተወጣጡ ባለሙያዎች በእሴት ሰንሰለት ዙሪያ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ከጥር 02-10/2011 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡ ሥልጠናው በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በብረታ ብረትና እንጨት ሥራ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኮንስትራክሽንና በሆቴሎች የእሴት ሰንሰለት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደተናገሩት ሥልጠናው የተክኖሎጂ ሽግግርን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለህብረተሰቡ ለማዳረስና ውጤታማ የቴክኖሎጂ ትስስርን ለመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስፋፋት ወደ ህብረተሰቡ ለማስተላለፍ እንዲሁም የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት ያለመ ነው፡፡ ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ ከአምራች ኢንደስትሪዎች፣ ከንግድና ኢንደስትሪ ጽ/ቤቶችና ከምርምር ማዕከላት ጋር በጋራ መስራት የማህበረሰቡን ችግሮች  በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል ያሉት ዶ/ር ቶሌራ ሥልጠናው  በዘርፎቹ ምርታማነትና ውጤታማነትን ከማሳለጥ አኳያም ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በኢኮኖሚክስ ት/ክፍል ረዳት ፐሮፌሰርና የዩኒቨርሲቲው BENEFIT REALIZE ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ አንደተናገሩት በአብዛኛው ምርቶች እሴት ሳይጨመርባቸው ለገበያ የሚቀርቡ በመሆናቸው አምራቹ ህብረተሰብ ማግኘት የሚገባውን ጥቅምና ትርፍ እያገኘ አይደለም ብለዋል፡፡ እንደ ዶክተሩ ገለፃ ከግብዓት እስከ ውጤት ድረስ በእያንዳንዱ ምርት ላይ እሴት መጨመር ለህብረተሰቡም ሆነ ለመንግስት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልፀው ምርቶች የእሴት ሰንሰለታቸውን ጠብቀው ለገብያ እንዲቀርቡ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሰልጣኞችና ባለድርሻ አካላት በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ከመጠቀም እንፃር ተገቢውን ትኩረት በመስጠት መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳተላይት ኢንስቲትዩት ኮሌጅ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንደስትሪ ትስስር ኢንስፔክሽን ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪና የኮሌጁ ም/ዲን አቶ ወርቅነህ ኃ/ሚካኤል እንደገለጹት በተቋማትና በአምራች ኢንደስትሪዎች መካከል በሚደረጉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎች ላይ ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል አንዱ የሆነውን የእሴት ሰንሰለት ችግርን በመፍታት በትስስሩ ውጤታማ ሥራዎችን በቅንጅት መስራት ለተቋማትም ሆነ ለማህበረሰቡ የሀብት ተጠቃሚነት ሚናው ጉልህ  ነው ብለዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው በሥራ ወቅት የነበራቸውን የአቅምና ግንዛቤ ክፍተት አንደቀረፈላቸውና ወደ ሥራቸው ሲመለሱ ባገኙት እውቀት ታግዘው ከወትሮው በበለጠ ተግተው ውጤታማ ሥራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ተሳታፊዎች በየዘርፉ የሚሰሩ የእሴት ሰንሰለት ሥራዎችን ያካተቱ አራት ንድፈ ሃሳቦችን ያቀረቡ ሲሆን በመጨረሻም  ለሰልጣኞች የተሳትፎ የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ ሥልጠናው ተጠናቋል፡፡