የዓለም ባንክ ከኢኮኖሚክስ ት/ክፍል ጋር  በመተባበር ‹‹Poverty and Household welfare in Ethiopia, 2011-2016›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ 7ኛውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሻሻል ሪፖርትን አስመልክቶ ዓመታዊ ዓውደ-ጥናት ጥር 29/2011 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካሂዷል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እንዲሁም ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ  እየጣረች ያለች ሃገር ናት በማለት በውይይቱ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ይህን ለማሳካት መንግስትና ማህበረሰቡ ለትምህርት ትኩረት በመስጠት እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ትልቅ የምርምር ተቋም ለመሆን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዘደንቱ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ የተሻለ ሥራ እየሰራ እንደሚገኝና ይህም መንግስት በሁሉም መስኮች የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሚያደርገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል ብለዋል፡፡
በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ ት/ክፍል ኃላፊ አቶ አፈወርቅ ብርሃኑ አውደ ጥናቱ የዓለም ባንክ በኢትዮጲያ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ባደረገው ጥናታዊ ሪፖርት ላይ ነባራዊና ሙያዊ አስተያየት በመካተት ሪፖርቱን የተሟላ በማድረግ መንግስትና ባለድርሻ አካላት የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ ሊወሰዱ በሚገቡ የመፍትሄ ሃሳቦች ዙሪያ የጋራ መግባባት መፍጠርንና በቀጣይም የእርስ በእርስ ሙያዊ ትስስር ማጎልበትን በማለም የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ቻይናና አሜሪካን የመሳሰሉ ያደጉ ሃገሮች የሚፈጥሩት የኢኮኖሚ ሩጫ ኢኮኖሚያቸው አነስተኛ በሆኑና ባላደጉ ሃገሮች ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም በማለት ጥናታዊ ተሞክሯቸውን ያካፈሉት በዓለም ባንክ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ማኔጀር Dr. Mathew A. Verghis እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2017/18 ዓለም ባንክ ባደረገው ጥናት ከ2003 እስከ 2007 ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ካሳዩት ሃገራት ተርታ ተሰልፋ እንደነበር እና እንደ ፈረንጆቹ አቆጣር ከ2016 ወዲህ  የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ቀደም ሲል ከነበረበት የ10.9 መቶኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ 7.7 መቶኛ ቀንሷል ብለዋል፡፡
የጥናት ውጤቱን ካቀረቡ ባለሙያዎች መካከል በኢትዮጲያ የማክሮ-ኢኮኖሚ ተመራማሪ ዶ/ር ዘሪሁን ጌታቸው እንደጠቀሱት ከጥቂት ዓመታት በፊት በእርሻው፣ በትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሁም በኢንደስትሪ ፓርኮች ውስጥ በነበረው የኮንስትራሽን ዘርፍ ዕድገት ኢኮኖሚውን ወደ ተሻለ ደረጃ የወሰዱ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በኢንደስትሪዎች እና በግብርናው ዘርፍ ምርታማ ከመሆንና ወደ ውጭ ከሚላኩ  ምርቶች ጋር  ተያይዞ ሰፊ ክፍተቶች መፈጠራቸው እንዲሁም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በመንግስት ኢንቨስትመንት ፖሊሲ ብቻ መመራቱና በሌሎችም የኢኮኖሚ እንቅፋቶች ምክንያት  ዕድገቱን ማስቀጠል አልተቻለም ብለዋል፡፡ አሁን ላይ መንግስት የውጭ ኢንቨስተሮችን ወደ ሃገር ውስጥ በመጋበዝ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘረፍ ላይ እንዲሰማሩና  ሃገሪቱ በምትፈልገው መጠን ምርቶችን እንዲያመርቱ በማድረግ ብሎም ኢኮኖሚውን ሊያሳድጉ የሚችሉ ሌሎች አማራጭ ስትራቴጂዎችን በመቀየስ እየሰራ መሆኑ አበረታች ተግባር መሆኑን  ተመራማሪው ጠቁመዋል ፡፡
የዓለም ባንክ ጥናትን መነሻ በማድረግ በሪፖርቱ እንደተገለፀው ሀገሪቱ ወደ ውጭ የምትልከው ጥሬ የግብርና ምርቶች ጥራትና ዋጋ መቀነስ፣ የካፒታል እቃዎች መጨመር፣ የዋጋ ንረት፣ የሥራ አጥነት ቁጥር መጨመር፣ የግለሰቦች የቤት ውስጥ ፍጆታ መጨመር፣ የግሉ ፋይናንስ ሴክተር ቁጥር መቀነስ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ኢኮኖሚውን መንግስት ብቻ መቆጣጠር፣ ሀገሪቱ መክፈል ከምትችለው በላይ ብድር መውሰድ፣ የአየር መዛባት፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲሁም መሠል ጉዳዮች  የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲቀንስ ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸው ተጠቁሟል ፡፡
የድሃው ህብረተሰብ ክፍል አኗኗርን የሚያሻሽሉ ፖሊሲዎችን ማውጣት፣ አምራች  ኢንደስትሪዎች ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ፣  የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና  ውጤቶች  አቅርቦትና ጥራት መጨመር፣ የግል ባለሃብቶችን አሳታፊ የደረገ የኢኮኖሚ ሥርዓት መዘርጋት የሚሉት ያሽቆለቆለውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲያገግም ለማድረግ በትኩረት ሊሰራባቸው የሚገቡ ተግባራት መሆናቸው በሪፖርቱ እና በተሳታፊዎች  የመፍትሄ ሀሳቦች ሆነው ቀርበዋል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች  ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በበኩላቸው የሀገር ኢኮኖሚ ደረጃን የተሻለ ለማድረግ መሠል ጥናትን መሠረት ያደረጉ ምሁራንን እና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ ውይይቶችን ማድረግ በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ክፍተቶች ላሉባቸው ኢትዮጵያን ለመሰሉ ሃገሮች ያለው ጠቀሜታ የላቀ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም  የሀገርን ልማት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ጥናትና ምርምሮች ላይ ትኩረት ያደርጋል ብለዋል፡፡
በሪፖርቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት መነቃቃት ቢታይበትም እየጨመረ የመጣውን የድሆች ቁጥር ለመቀነስ ብሎም ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉና በጥናት በተደገፉ ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ የተጠቆመ ሲሆን በውይይቱ ከዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ፅ/ቤት፣ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአርባ ምንጭ ከተማና ከሌሎች መ/ቤቶች የተወጣጡ ባለድርሻ  አካላት  ተሳትፈዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት