የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ የዩኒቨርሲቲውን የ2011 ዓ/ም በጀት ዓመት የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማን ጨምሮ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ የካቲት 9/2011 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ዶ/ር ይናገር ደሴ  እንደገለፁት ግምገማው በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ በሁሉም ዘርፎች የታቀዱ ተግባራት አፈፃፀም በመፈተሽ ዝቅተኛ አፈፃፀም በታየባቸው መስኮች በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ በማድረግ በመማር ማስተማርም ሆነ በሌሎች የዩኒቨርሲቲው አበይት ተልዕኮዎች ውጤት ለማስመዝገብ ይረዳል ብለዋል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተመለከተው በመማር ማስተማር ዘርፍ የት/ት አግባብነትና ጥራትን ለማሳደግ ኮርሶች ሙሉ በሙሉ በሞጁላር ሥርዓተ መሰጠታቸው፣ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ የት/ት መስኮች መከፈታቸው፣ ለተማሪዎች የመማሪያ አካባቢዎችን ምቹ ከማድረግ አንጻር በየካምፓሱ የተለያዩ ሥራዎች መሰራታቸው፣ የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች መማሪያ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ስማርት እንዲሆኑ መደረጉ እንዲሁም በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ዓመታዊ የምርምር ሥራዎች ዳሰሳ አውደ ጥናት መካሄዱ፣ በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች የተሠሩ ምርምሮች በታወቁ ዓለም አቀፍ ጆርናሎች መታተማቸው እና ነፃ የህግ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ሦስት ተጨማሪ ማዕከላት ተከፍተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው በግማሽ ዓመቱ ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
በተጨማሪም የሴት መ/ራንን የምርምር አቅም ለማሳደግ ስልጠና መሰጠቱ፣ ከውጪ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ የምርምር ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑ፣ በተመረጡ የተማሪዎች አገልግሎት መስጫ ህንፃዎች ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች መግቢያና መውጫ ራምፖች መገንባታቸውና፣ የውጪ አካላት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር እንዲሰሩ የሚያግዙ ተቋማዊ መረጃዎች በተለያዩ  ሚዲያዎች እንዲሰራጩ መደረጋቸው በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ 
የበጀት ፍሰት በተፈለገው መጠን አለመሆን፣ የግንባታዎች መዘግየት፣ የግዥዎች መስተጓጎል፣ የተሸከርካሪ እጥረት፣ የአስተዳደር ሠራተኞች ነጥብ ምዘና ሥርዓት (JEG) ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ውጤትን በወቅቱ ያለማሳወቅ፣ የአዲስ ተማሪዎች ቅበላ ቁጥር ከእቅድ በላይ መሆኑ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጫና መፍጠር፣ ሴቶችን የማብቃት ሥራ በሚጠበቀው ደረጃ አለመከናወን በግማሽ ዓመቱ የታዩ ውስንነቶች መሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
ሰላማዊ መማር ማስተማር ሁኔታን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከተማሪ አደረጃጀቶች፣ ከአከባቢው መስተዳድርና ሕብረተሰብ ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር፣ በተማሪዎች መካከል የኢትዮጵያዊነት፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብና የመቻቻል አስተሳሰብን ሊያጎለብቱ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ መሥራት፣ የትምህርት ጥራትና መልካም አስተዳደር ፎረም ውይይቶችን ከተማሪዎች፣ ከመምህራንና ከአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ጋር ማካሄድ እንዲሁም ከውይይቶች ግብዓት በመውሰድ ክፍተቶችን ማስተካከል በሚያስችሉ አግባቦች ላይ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡
በዕለቱ የባህሪ ማሻሻያ ማዕከል ማቋቋም፣ የባህል ብዝሃነትና ቋንቋ ምርምር ማዕከል ማቋቋም፣ የተሻሻለውን የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ መዋቅር ማሻሻያ ማጽደቅና በመሳሰሉት አጀንዳዎች ላይ በስፋት ውይይት ተደርጓል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም ከቦርድ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በሚመለከታቸው የበላይ አመራር አካላት ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን ውጤታማ አፈፃፀሞችን ይበልጥ ማጎልበትና ዝቅተኛ አፈፃፀም በታየባቸው የሥራ ዘርፎች ሁሉም አካላት ትኩረት ሰጥተው በቁርጠኝነትና በመግባባት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አባላቱ አሳስበዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው አቅም በላይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ቦርዱ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመሆን ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግም አሳውቋል፡፡
በሌላ በኩል የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ አባላት ከውይይቱ በኋላ በዩኒቨርሲቲው ባሉ ካምፓሶች እየተካሄዱ የሚገኙ የግንባታ እና ሌሎችንም የልማት ሥራዎች ተዘዋውረው ጉብኝተዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት