አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የጫሞ ሐይቅን ከአደጋ ለመታደግ በተጀመረው ፕሮጀክት አፈፃፀምና በኤልጎ ተፋሰስ መሬት መሸርሸር ዙሪያ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን ምርምር ሂደትና ውጤት አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር የካቲት 13/2011 ዓ/ም ውይይት ተካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

በፕሮጀክት አፈፃፀም ሪፖርቱ እንደተመለከተው ዩኒቨርሲቲው ከፓርኩና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የሐይቁን
ብዝሃ-ህይወት በዘላቂነት ለመጠበቅ፣ የሀይቁን የዓሳ ሀብት ወደ ነበረበት ለመመለስና ከመጠን ያለፈ ዓሳ ማስገርን ለመከላከል የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ሥራውን  ከጀመረበት ከግንቦት 2010 ዓ/ም ጀምሮ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል 100 ሄክታር የሚያህል የሀይቁን ክፍል በመከለልና ሀገር በቀል እፅዋትን በመትከል በተደረገ ጥበቃ የዓሳው ቁጥር ዕድገት ማሳየት እንዲሁም የሀይቁ buffer zone (በፈር ዞን) ጥናት መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

ሐይቁ በከፍተኛ ሁኔታ በደለል አፈር እየተሞላ መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ፋሲል በዚህ ረገድ በሐይቁ ላይ ብቻ የሚሠሩ ሥራዎች ሐይቁን ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ በቂ አይደሉም ብለዋል፡፡ እንደ ተመራማሪው ገለፃ ሐይቁን ከተፋሰሱ ለይቶ ማየት ስለማይቻል ሐይቁን ለማዳን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ተፋሰሱ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራቱ አስፈላጊ ነው፡፡

በመሆኑም በፕሮጀክቱ አማካይነት የሐይቁ ዋነኛ ተፋሰስ በሆነው የኤልጎ ተፋሰስ የአፈር መሸርሸር ችግርና መጠኑን ለማወቅ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ምርምሩ በዋናነት ኃይቁን ከደለል ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ጋር ተያይዞ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከመገባቱ በፊት ችግሮችን ሳይንሰዊ በሆነ መንገድ ለይቶ መፍትሄ ለማበጀት እንዲሁም ለሌሎች በዘርፉ መሥራት ለሚፈልጉ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትክክለኛውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንዲሠሩ ያግዛል፡፡

ዶ/ር ፋሲል የምርምሩን ውጤት ባቀረቡበት ወቅት እንዳብራሩት በአካባቢው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች በብዛት ሲሠሩ ቢስተዋልም ሥራው ሳይንሳዊና በጥናት ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ ከጥቂት ቦታዎች በስተቀር ውጤት አላሳየም፡፡ በጥናቱ ለየትኛው አካባቢ ምን ዓይነት የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ እንደሚያስፈልግ የተለየ ሲሆን ይህም ማንኛውም አካል ሳይቸገር ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ የሚያግዝ መሆኑንና የጥናቱን ግኝቶች መሠረት በማድረግ በተፋሰሱ የላይኛው ክፍል በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ የሚሠራ ይሆናል፡፡

የአፈር መሸርሽርን ለማጥናትና ምን ያህል አፈር በየጊዜው እንደሚሸረሸር ለማወቅ የአፈሩን ተፈጥሮ፣ የዝናብ ስርጭት፣ የመሬቱን ተዳፋትነት፣ የዕፅዋት ወይም የደን ሽፋን እና የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች በምን ያህል ደረጃ እየተሠሩ መሆናቸውን ማጥናት አስፈላጊ በመሆኑ ምርምሩ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መሠራቱን የገለፁት ዶ/ር ፋሲል በዚህ ረገድም በተፋሰሱ በዝናብ ስርጭት፣ በአፈሩ ተፈጥሮ፣ በመሬቱ ተዳፋትነት፣ በእፅዋትና ደን ሽፋን ምክንያት አፈራቸው የሚሸረሸሩ ቦታዎች መለየታቸውንና በተለዩ በታዎች ምን ዓይነት የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ መሠራት እንዳለበት በጥናቱ መለየቱን ተናግረዋል፡፡

ከደንና የእፅዋት ሽፋን ጋር ተያይዞ በጥናቱ በቀረበው መረጃ መሠረት በኤልጎ ተፋስስ እ.ኤ.አ በ1988 ዓ/ም በተፋሰሱ ከሚገኘው መሬት 4,261 ሄክታር መሬት በደን ተሸፍኖ የነበረ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ከአስር ዓመት በኋላ ቁጥሩ በግማሽ ቀንሶ 2,122 ሄክታር ብቻ በደን የተሸፈነ መሆኑ ታወቋል፡፡ በአጠቃላይ እ.ኤ.አ ከ1988-2015 ዓ/ም ባሉት 27 ዓመታት ውስጥ 47% የሚሆነው የደን ሽፋን ከተፋሰሱ የጠፋ መሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡

በሐይቁ ዙሪያ የሚገኘው ረግረጋማ ቦታ (Wet Land) እንዲሁም እንደ ደንገል ያሉ እፅዋት የሐይቁ ማጣሪያ ኩላሊቶች ናቸው ያሉት ዶ/ር ፋሲል ነገር ግን በጫሞ ሐይቅ  እ.ኤ.አ ከ1988-2015 ዓ/ም ባሉት 27 ዓመታት 75% የሚሆነው ረግረጋማ ቦታ ለእርሻና ለሌሎች ተግባራት መዋሉ በጥናቱ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ደለል አፈር ያለ ከልካይ ወደ ሐይቁ እንዲገባ ማድረጉንና ይህም ለሐይቁ ሌላኛው ስጋት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት እንደተገለፀው እስካሁን ባለው የጥናቱ ሂደት ምን ያህል አፈር በየዓመቱ እየተሸረሸረ ወደ ሐይቁ እንደሚገባ እንዳልታወቀ የተጠቆመ ሲሆን ሥራው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ስሌቱ የሚታወቅ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በተፋሰሱ ላይ የተጀመረው ሥራ የጋራ እንዲሆንና ዘላቂነት እንዲኖረው ባለድርሻ አካላቱ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው መሥራት ይገባቸዋል ሲሉ ተወያዮች አበክረው አሳስበዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ በIUC ፕሮጀክት፣ GIZ በተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ የጀርመን ድርጅት፣ በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ፣ በጋሞ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ፣ በጋሞ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ መምሪያ፣ በአርባ ምንጭ ዙሪያና በቦንኬ ወረዳ ትብብር የሚሠራ ሲሆን በዞን አስተዳደር ደረጃም ለዚሁ ዓላማ ሲባል የማኔጅመንትና ቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሠራ ይገኛል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት