እንግሊዝኛ ቋንቋን ከ ICT ጋር አቀናጅቶ የማስተማር ስነ- ዘዴ አዲስ ፕሮጀክት ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

ICTን ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ጋር በማቀናጀት በICT መሣሪያዎች  የቋንቋውን የመማር ማስተማር ሂደት የተሻለ በሚያደርግ  አዲስ ፕሮጀክት ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ፣ ከአርባ ምንጭና ከሣውላ 2ኛ ደረጃና መሠናዶ ት/ቤቶች እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የካቲት 16/2011 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እንደገለጹት የውይይቱ ዓላማ ICTን ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ጋር በማቀናጀት በቋንቋው ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት በሚያስችል እንዲሁም ፕሮጀክቱን በማስጀመር በቀጣዩ  ሊከናወኑ በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ  ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ መድረስ ነው፡፡ የመማር ማስተማሩ ሂደት ጥራትና አግባብነቱ  በምርምር ላይ የተደገፈ ሊሆን ይገባል ያሉት ዶ/ር ስምዖን ሠልጣኞች ከዩኒቨርሲቲው የሚያገኙትን እውቀትና ክህሎት  ከተማሪዎቹ አልፎ ወደ ማኅበረሰቡ በማሸጋገር የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ዙሪያ ገለፃ የሰጡት የተቋማዊ ጥራት ማበልፀጊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ያደጉ አገሮች የማደጋቸው ምስጢር ዘመኑ ያመጣቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች  በአግባቡ በመጠቀማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንግሊዝኛ  ቋንቋ የዓለም መግባቢያ ቋንቋ ከመሆኑም ባሻገር የማስተማሪያ ቋንቋ ሆኖ በየት/ቤቶቻችን እየተሰጠ ነው ያሉት ዶ/ር ተስፋዬ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በኢትዮጵያ በሚገኙ ት/ቤቶች ውስጥ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መ/ራን ክህሎታቸውን ለማሳደግ የሚያደርጉት ጥረት አናሳ በመሆኑ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎታቸው አጥጋቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከ2011 ዓ/ም እስከ 2013 ባሉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ተግባራዊ የሚሆነው ፕሮጀክት በICT መሣሪያዎች አጠቃቀም ላይ በዩኒቨርሲቲው በልህቀት ማዕከልነት በተመረጡ ት/ቤቶች ለሚገኙ መ/ራን ስልጠና በመስጠት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ጥራት ላይ ያመጣው ለውጥ ታይቶ በቀጣይ በተማሪዎች የICT መሣሪያዎች አጠቃቀምን የተመለከተ እና ጥናትን  መሠረት ያደረገ  አዲስ ፕሮጀክት ተግባራዊ ይሆናል፡፡

የICT መሣሪያዎችን ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ጋር ማቀናጀት የICT መሣሪያዎችን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያግዙ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ቃላትን ከማሳወቁ ባሻገር ጥራት ያለው የትምህርት ዕቅድ ለማቀድ፣ በኦዲዮና ቪዲዮ የታገዘ ትምህርት ለመስጠት፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፊደላትን ለመማር እንዲሁም ለመምህሩና ለተማሪው የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሻሻልና በአጠቃላይ የቋንቋውን ክህሎት ለማሳደግ ያስችላል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ዌብሳይት፣ ኮምፒውተር፣ ሞባይል ቀፎዎች፣ ላፕቶፕ፣ ጎግል፣ ፌስቡክ እንዲሁም መሰል የ21ኛው ክ/ዘመን የICT መሣሪያዎችንና ውጤቶችን ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማር ጋር በማቀናጀት የቋንቋውን ክህሎትና የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ከቴክኖሎጂው ጋር ለመጓዝ እድል የሚፈጥር በመሆኑ አግባብነት ያለው የአጠቃቀም መመሪያና ደንብ ሊወጣለት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡   
በተጨማሪም ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለሠልጣኝ መ/ራን መስጠት፣ ተቀናጅቶ መሥራት፣ በሥልጠናው የICT መ/ራንን ማካተትና ለሠልጣኞች እውቅና መስጠት በተሳታፊዎች ከቀረቡ የመፍትሄ ሃሳቦች መካከል ናቸው፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች፣ ከጋሞና ጎፋ ዞኖች የተወጣጡ የICT መ/ራን፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ት/ክፍል ተጠሪዎች፣ ርዕሳነ/መ/ራን፣ ም/ርዕሳነ/መ/ራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ፡፡