123ኛው የአድዋ ድል በዓል በዩኒቨርሲቲው ተከበረ

123ኛው የአድዋ ድል በዓል የተለያዩ የታሪክ ምሁራን በተገኙበት የካቲት 23/2011 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው በድምቀት ተከብሯል፡፡
በዕለቱ ‹‹የጦርነቱ መነሻና የጦርነቱ ገጽታዎች››፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከቅኝ ገዢዎች እንዴት ነጻነቷን ጠበቀች››፣ ‹‹የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን የአንድነት፣ የጀግንነትና የነጻነት ማኅተም›› እና ‹‹የጦርነቱ ውጤቶችና ትሩፋቶች›› በሚሉ 3 ርዕሶች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የአድዋ ድል መልካም ተሞክሮን ልንገበይበት የሚያስችለን የኢትዮጵያዊያን ታሪካዊ ድል ብቻ ሳይሆን ለመላው የጥቁር ህዝቦችና ለተቀረውም ዓለም የድል ነጸብራቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህንንም በመዘከርና ለልጆቻችን በማስተማር ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ ልናደርገው እንደሚገባን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

የማኅበረሰብና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ በበኩላቸው አድዋ የጀግኖች አባቶቻችን የአንድነት ትስስርን ያጠናከረና የአልደፈር ባይነት ወኔን ሰንቀው ለአንድ የጋራ ዓላማ እንዲቆሙ ያደረገ በመሆኑ ለሌሎች ለተጨቆኑ ህዝቦች ሁሉ የሠላምና የነፃነት ተምሳሌት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የአድዋ ድል አፍሪካዊያን አገራቸውን ከቅኝ ገዢዎች እንዴት ነጻ ማውጣት እንደሚችሉ ያሳየና ነጮች ለአፍሪካዊያንና ለመላው ጥቁር ህዝቦች ያላቸውን ዝቅተኛ አመለካከት የቀየረ መሆኑን የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር በለጠ በላቸው አብራርተዋል፡፡ ዶ/ር በለጠ ያደረጉት ንግግር የአድዋ ምንነት፣ የአድዋ በዓል ባለቤትነት፣ የአድዋን የቤት ሥራ ያለመሥራትና አድዋ የኢትዮጵያዊነት የመላው ጥቁር ህዝብ ማንነትን የቀረጸ ድል ነው በሚሉ ጭብጦች ዙሪያ ትኩረት አድርጓል፡፡

እንደ ዶ/ር በለጠ ማብራሪያ አድዋ ነጻነታችንና አንድነታችንን ቀርጿል ብንልም በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያውያን ከአድዋ የነጻነት ትርጉም ወጥተን ዝቅ ያለ ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ ከአድዋ የተማርነው ሉዓላዊነትን፣ ህብረብሄራዊነትን እና ነጻነትን ጠብቆ ማቆየትን ቢሆንም በራሳችን አመለካከትና ማንነት ላይ መመሥረት ሲገባን የፖለቲከኞችን ሀሳብ ተቀብለን ስናንፀባርቅ እና የጎጠኝነትና የብሄርተኝነትን አካሄድ ስናስፋፋ ቆይተናል፡፡ ይህም ለአገራዊ እሳቤያችን ያለን ቦታ ዝቅ እንዲል ያደረገና የፖለቲካ አመለካከታችን እንዳልዳበረ ያመላከተ በመሆኑ ጀግኖች አባቶቻችን በአድዋ የሠሩትን ጀግንነት በኢኮኖሚው ዘርፍም ለመድገም ተባብሮና ጠንክሮ የመሥራትን ታሪክ እንደ መነሻ መጠቀም እንችላለን፡፡ አድዋ የፖለቲካ እንጂ የኢኮኖሚ ነፃነትን ያላረጋገጠ በመሆኑ ይህንን ማሳካት የዚህ ትውልድ የ123 ዓመታት ያልተሠራ የአድዋ የቤት ሥራ መሆኑን ዶ/ር በለጠ ተናግረዋል፡፡

የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ካሱ ጡሚሶ የድል በዓሉን መዘከራችን ለብሄራዊ ክብርና ሉአላዊነት በጋራ የመቆምና በጋራ ሠርቶ ለውጤት መብቃትን አስተምሮናል ብለዋል፡፡ የጀግኖች አባቶቻችን የጋራ ሥራ አገራችን በያዘችው የለውጥ ሂደት በሌሎች የልማት ሥራዎችም ቀጥሎ ለመጪው ትውልድ የአባቶቻችንን አደራ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅብንም ተናግረዋል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየቶች በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የሚያራምዱት የጎጠኝነት፣ የብሄርተኝነትና የጠባብነት አካሄድ ኢትዮጵያ የቀድሞ አንድነቷን ይዛ እንዳትቀጥል እንዲሁም የኢኮኖሚው እድገት እንዲኮስስና ካለበት ደረጃ እንዳያድግ አድርጓል፡፡ አባቶቻችን የአገራችንን አንድነትና ነጻነቷን ጠብቀው እንዳቆዩት ሁሉ እኛም አንድነታችንን አጠናክረን መዝለቅ እና ለኢኮኖሚ እድገቱ መሻሻል ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥተን መሥራት አለብን ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ከጋሞ ዞንና ከአርባ ምንጭ ከተማ የመጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች እናትና አባት አርበኞች እንዲሁም ተማሪዎች በዓሉን ታድመዋል፡፡