የምርምር ዳይሬክቶሬት ከሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ለዩኒቨርሲቲው ነባርና አዲስ ለተቀጠሩ ሴት መ/ራን  ለምርምር ሥራ አጋዥ በሆኑ Grand Project Proposal Writing Skill፣ Thematic Research Proposal Writing Skill፣ Scientific Manuscript እና Software Training Theoretical Background ላይ ከመጋቢት 17-20/2011 ዓ/ም ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በመክፈቻ ንግግራቸው ሴት መ/ራን ጥበብን በመፈለግ፣ ግልፀኝነትን በማዳበርና የተደበቀ ማንነታቸውን በማውጣት እንዲሁም እውቀታቸውን ከቴክኖሎጂው ጋር በማዋሃድ ከወንዶች እኩል  በምርምር ዘርፍ የተሻለ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ እንደገለፁት የስልጠናው ዓላማ ሴት መ/ራን ከመማር ማስተማር ሥራ ጎን ለጎን ከወንዶች እኩል በምርምር ሥራ ተሳታፊ እንዲሆኑ አጋዥ የምርምር እውቀት ላይ ግንዛቤ መስጠት ነው፡፡

በትምህርት ተቋማት ምርምር እንደ አንድ ኮርስ በንድፈ ሀሣብ ቢሰጥም የተማሩትን ትምህርት ተግባር ላይ ከማዋል አንፃር ድክመት ይታያል ያሉት ዶ/ር ተሾመ በተለይ ሴት መ/ራን ተመራማሪ የመሆን ዕድላቸውን የተሻለ ለማድረግ በምርምር ላይ የማንበብና የመፃፍ ክሂሎትን በማዳበር ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

በህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የህክምና ላቦራቶሪ ትምህርት ክፍል የሂዩማቶሎጂና ኢሚኒዮ ሂዩማቶሎጂ መ/ርት ገሊላ ቢረሳው  ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ ካለው የተዛባ አመለካከትና የሥራ ክፍፍል የተነሳ በሚፈጠር የሥራ ጫና ሴቶች ነገሮችን የሚያዩበትና የሚረዱበት መንገድ ከወንዶቹ እኩል አይደለም ብለዋል፡፡ ስልጠናው ማኅበረሰቡ ለሴቶች ያለውን አሉታዊ አመለካከት በመቀየር የሴት መ/ራንና ተመራማሪዎችን ቁጥር ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አገሪቱ ከወንዶች የምትጠብቀውን እውቀት ወይም ሁለንተናዊ ድርሻ ከሴቶችም ትጠብቃለች ያሉት መ/ርት ገሊላ በመሆኑም ሴቶች ካሉበት የተሻለ እንዲጓዙ ወንዶች ያላቸውን እውቀት በማካፈል እንዲሁም ጫናዎችን በመጋራት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ ሴት መ/ራን በትምህርት ዓለም ያገኙትን እውቀት ከምርምር እውቀት ጋር ማዋሃድ፣  የሴቶችን ብሎም የማኅበረሰቡን የኑሮ ደረጃ የተሻለ የሚያደርጉ ምርምሮችን መሥራት እና ከወንዶች እኩል የተመራማሪነት እውቀታቸውን ማዳበር እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ሴት መ/ራን ያላቸው ዝቅተኛ ተነሳሽነት፣ በማኅበራዊ ህይወታቸው ውስጥ ያላቸው የኃላፊነት ጫና እንዲሁም ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን ከወንዶች እኩል በምርምሩ ዘርፍ ተሳታፊ እንዳይሆኑ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ናቸው፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሴት ተመራማሪ መ/ራን በምርምር ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም ወንድ ተመራማሪ መ/ራን ካሉበት የ40 በመቶ ዝቅተኛ የምርምር ተሳትፎ ባነሰ መልኩ የሴት ተመራማሪ መ/ራን 28 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡       
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት