በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሜካኒካልና ፕሮዳክሽን ኢንጂነሪንግ ፋካልቲ የፕሮዳክሽን ኢንጂነሪንግ ፕሮግራም የማስተዋወቂያ (Promotion) ወርክሾፕ መጋቢት 21/2011 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ በወርክሾፑ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ የግልና የመንግሥት አምራች ኢንደስትሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ ወርክሾፑ በዩኒቨርሲቲው አዲስ እና በአገሪቱ የመጀመሪያ የትምህርት መስክ የሆነውን ፕሮዳክሽን ኢንጂነሪንግ ለቀጣሪ ኢንደስትሪዎች ከማስታዋወቅ ባሻገር በዩኒቨርሲቲውና በአምራች ኢንደስትሪዎች መካካል ያለውን ትስስር ለማጠናከር ያለመ ነው ብለዋል፡፡ የወርክሾፑ ተሳታፊ አምራች ኢንደስትሪዎችም የዩኒቨርሲቲው አምባሳደር በመሆን በራሳቸው ኢንደስትሪም ሆነ በሌሎች በመላው አገሪቱ በሚገኙ መሰል ተቋማት የትምህርት መስኩን ለማስተዋወቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ መንግሥት በአገሪቱ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ለምታከናውናቸው ሥራዎች ለኢኮኖሚው የተለያዩ መስኮች ከፍተኛ ባለሙያዎችን ማፍራት ወሳኝ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ይህንን መነሻ በማድረግ በርካታ ምሁራንን በተለያዩ መስኮች እያፈራ ይገኛል ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዳምጠው ገለፃ አገሪቱ ከግብርና መር ወደ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር በምታደርገው ጥረት ውስጥ በኢንደስትሪው ገብተው ሊሠሩ የሚችሉ በፕሮዳክሽን ኢንጂነሪነግ እና መሰል የትምህርት መስኮች የሚመረቁ ባለሙያዎች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በወርክሾፑ የሚደረገው ውይይትም ፕሮግራሙን ለማሻሻልና በመስኩ ጥራት ያላቸውን ምሁራን ለማፍራት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ፕላንና ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ገመቹ በሰጡት ሃሳብ መንግሥት በዕውቀት የሚመራ የኢንደስትሪ ልማት ስትራቴጂ እንደሚከተልና ከዚህ በኋላም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሠራ ገልፀዋል፡፡ የፕሮዳክሽን ኢንጂነሪንግ ምሩቃን ሥራ አናገኝም የሚል ስጋት ውስጥ ሊገቡ አይገባም ያሉት ዳይሬክተሩ ያለ ፕሮዳክሽን ኢንጂነሮች የሚለማ የኢንደስትሪ ፓርክም ሆነ አምራች ኢንደስትሪ አይኖርም ብለዋል፡፡ አሁን ላይ መንግሥት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየገነባቸው በሚገኙና ተገንብተው ሥራ በጀመሩ ፓርኮች እንዲሁም በሌሎች አምራች ኢንደስትሪዎች የመቀጠር ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በመዝጊያ ንግግራቸው እንደገለጹት በወርክሾፑ ስኬታማ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን ከአምራች ኢንደስትሪዎች በተገኙ ግብዓቶች መሠረት በፕሮግራሙ ላይ ማስተካከያዎች በማድረግ ጥራት ያላቸው ምሩቃንን ለማፍራት ዩኒቨርሲቲው ይሠራል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርን ለማጠናከር ሁለቱም አካላት በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የሜካኒካልና ፕሮዳክሽን ኢንጂነሪንግ ፋካልቲ ዲን አቶ አትክልት ሙሉ ከዚህ ቀደም በመረጃ ክፍተትና ከመስኩ አዲስ መሆን ጋር ተያይዞ በተማሪዎችና በዩኒቨርሲቲው መካከል የተወሰኑ ውዝግቦች መፈጠራቸውን አስታውሰው ውዝግቦቹ በውይይት አንደተፈቱና በአገሪቱ ሁሉም ጫፎች ወደሚገኙ አምራች ኢንደስትሪዎች ልዑክ ቡድን በመላክ ፕሮግራሙን የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ አምራች ኢንደስትሪዎችም ከዚህ ቀደም የፕሮዳክሽን ኢንጂነሪንግ ምሩቃን ባለመኖራቸው መቸገራቸውንና በሌሎች የኢንጂነሪንግ መስኮች ለተመረቁ ተጨማሪ ሥልጠና በመስጠት እየተጠቀሙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ቀጥታ በፕሮዳክሽን ኢንጂነሪንግ የተመረቁ ባለሙያዎችን የሚያገኙ መሆኑ አምራች ኢንደስትሪዎችን እንዳስደሰታቸው አቶ አትክልት ተናግረዋል፡፡

በወርክሾፑ የተለያዩ አምራች ኢንደስትሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ መምህራና ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በመጨረሻም የሜካኒካልና ፕሮዳክሽን ኢንጂነሪንግ ቤተ-ሙከራዎችና ወርክሾፖች ጉብኝት ተደርጓል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት