በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹Ethiopia Debates›› በሚል መሪ ቃል ‹‹Arba Minch University Debate Club›› የተሰኘ የውይይትና የክርክር ክበብ መጋቢት 21/2011 ዓ/ም በይፋ ተቋቁሟል፡፡ ክበቡ CENTERE FOR COMMUNITY DEVELOPMENT በተሰኘ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅትና በአሜሪካ ኤምባሲ የሚደገፍ ነው፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

በምሥረታ ፕሮግራሙ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እንደገለፁት የሀሳብ ብዝሃነትን ለማስተናገድ በሰለጠነ መንገድ የሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች ኃላፊነት የሚሰማው ማኅበረሰብ ለመፍጠር ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ የክበቡ መመሥረት የተማሪዎችን የመናገር ነፃነት ከማጎልበቱም ባሻገር የመማር ማስተማሩ ሥራ ሠላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን አጋዥ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል፡፡

የማኅበራዊ ሣይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ በበኩላቸው የክበቡ መመሥረት በራሳቸው የሚተማመኑና ሀሳባቸውን በአግባቡ መግለጽ የሚችሉ ተማሪዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ ገልፀዋል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የሀሳብ ብዝሃነትን ማስተናገድ ባልጎለበተበት አገር በግልፅ ውይይትና ክርክር የሚደረጉባቸው መድረኮች መመቻቸታቸው ተማሪዎች በውይይትና በንግግር የሚያምኑና የሀሳብ ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችሉ እንዲሆኑ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የሴንተር ፎር ኮሚዩኒቲ ዴቨሎፕመንት ኤክሲኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ መላኩ አየነው እንደተናገሩት ፕሮግራሙ በአሜሪካ ኤምባሲ የሚደገፍና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በ14 ዩኒቨርሲቲዎች እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልፀው ክበቡ የተማሪዎችን የክርክር፣ የውይይትና የተግባቦት ክሂሎት በማሳደግ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የትልልቅ ሀሳቦች መፍለቂያ እንጂ ተማሪዎች በትንንሽ የሀሳብ ልዩነቶች የሚጋጩባቸው ቦታዎች መሆን የለባቸውም ያሉት ዳይሬክተሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለአገርና ለማኅበረሰቡ የሚጠቅሙ ትልልቅ ሀሳቦች አፍላቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል፡፡

ክበቡ በዋናነት በማኅበራዊ ሣይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ እና በኢንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መምህራን የሚደገፍ ሲሆን በሁሉም ካምፓስ የሚገኙ ተማሪዎች መሳተፍ ይችላሉ፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት