በኢንስቲትዩቶቹ ምቹ የመማር ማስተማር አካባቢ ለመፍጠር የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ

በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ እና ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ መፀዳጃ ቤቶች በመጠገን፣ የመንገድ መብራት ዝርግታ እና የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ በማካሄድ እንዲሁም ላቦራቶሪዎችንና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎችን በማሻሻል አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡

የኢንስቲትዩቶቹ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ያሊሾ ግርማ እንደተናገሩት የአንድ ጥልቅ ጉድጓድ የመስመር ዝርጋታ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ በተማሪዎች እና መምህራን መኖሪያ አካባቢ የነበረው የውኃ አቅርቦት ችግር ተቀርፏል፡፡ በመማሪያ ክፍሎች እና በቢሮዎች አካባቢ አገልግሎት የማይሰጡ መጸዳጃ ቤቶች በመጠገናቸውም የመጸዳጃ ቤት ችግር እንዲቀንስ አድርጓል፡፡

ለመምህራንና ለአስተዳደር ሠራተኞች ምቹ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር ከዚህ ቀደም ተዘግቶ የነበረው ሉሲ ካፍቴሪያ በአዲስ መልክ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን በቀጣይም አንድ ተጨማሪ ሬስቶራንት ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑን አቶ ያሊሾ ገልጸዋል፡፡ በግቢ ውስጥ የሚታየውን የፀጥታ ችግር ለመቅረፍና የሠራተኞችን ደህንነት ለማስጠበቅ በተማሪዎች እና መምህራን መኖሪያ አካባቢ የመንገድ መብራት ዝርጋታ ተከናውኗል፡፡ በተጨማሪም ከተማሪዎች መግቢያ በር እስከ ሲነጣ በር ያለው የመንገድ መብራት ተጠናቆ አገልግሎት ላይ በመሆኑ ከተማሪዎች ሲቀርብ ለነበረው ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኮምፒውተርና የሃይድሮሊክስ ላቦራቶሪዎች፣ የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከሮች፣ ለኃይል ማመንጫነት የሚውሉ የማስተማሪያ መሣሪያዎች፣ ግብዓታቸው ተሟልቶ በውኃ እና ፍሳሽ መስመር ምክንያት ያለ አገልግሎት ተዘግተው የነበሩ ላቦራቶሪዎች እንዲሁም ለተማሪዎች መዝናኛ ተገንብተው በመብራት እጥረት አገልግሎት የማይሰጡ ቦታዎች አስፈላጊው እድሳት፣ ጥገና፣ ማስተካከያና የመብራት መስመር ዝርጋታ ተደርጎላቸው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

በተለምዶ በማዘር ህንፃ (B -301) ጀርባ ያለውን ቦታ ለተማሪዎች መዝናኛ ለማድረግ የችግኝ ተከላ እና የማስዋብ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲውን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል አመራሩና ሠራተኞች በቁርጠኝነት እየሠሩ መሆኑን አቶ ያሊሾ ተናግረዋል፡፡

(ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት)