ዩኒቨርሲቲው ከግብርና ሣይንስ፣ ከተፈጥሮ ሣይንስ እና ከህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጆች የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከመጋቢት 28 – 29/2011 ዓ/ም 6ኛውን ሣይንስ ለዘላቂ ልማት አገራዊ ዓውደ ጥናት አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ እንደገለጹት የዓውደ ጥናቱ ዓላማ ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸውን ሣይንሳዊ የምርምር ሥራዎች በዘርፉ ምሁራን በማስተቸት የእውቀትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግና የእርስ በእርስ ትስስር ለማጠናከር ነው፡፡ ዓውደ ጥናቱ ለማኅበረሰቡም ሆነ ለአገሪቱ ዘላቂ ልማት ያለው ፋይዳ የላቀ ነው ያሉት ዶ/ር ተሾመ ተመራማሪዎች ከዘልማዳዊ አሠራር በመውጣት የሚያከናውኗቸው የምርምር ሥራዎች የማኅበረሰቡን ችግር በተግባር የሚፈቱ ሊሆኑ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ 320 ምርምሮችን እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ምርምር መንግሥትና ማኅበረሰቡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚጠብቋቸው ዋና ዋና ተግባራት አንዱ ነው፡፡ ተመራማሪዎች ምርምር ከማከናወን ባሻገር ከሰው ልጆች ህይወት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሁለንተናዊ ጉዳዮችን በመለየት ለማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ አሁን ላይ ያለው የምርምር ሥራ ሁኔታ የማኅበረሰቡን ችግር ከመፍታት አንጻር እና አገሪቱ ካስቀመጠችው የልማት ግብ ጋር ሲነፃፀር አጥጋቢ የሚባል አይደለም ያሉት ዶ/ር ዳምጠው አበረታች ሥራዎችን መነሻ በማድረግ ተመራማሪዎች የተሻለ ሊሠሩ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የምሁራንን መጠንና ጥራት ከፍ በማድረግ፣ አዳዲስ የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን በመክፈት፣ የምርምር ማዕከላትን በማቋቋም እንዲሁም ዓመታዊ የምርምር በጀትን በማሳደግ ከመማር ማስተማር ባሻገር በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ዩኒቨርሲቲው የተሻለ እየሠራ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ዳምጠው በቀጣይም የአገሪቱን የልማት ራዕይ ለማሳካት የተመራማሪዎችን አቅም በመገንባት ችግር ፈቺ ምርምሮችን እንዲያከናውኑ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በበኩላቸው አገሪቱ የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት ብትሆንም ከሰው ልጆች የአኗኗር ሁኔታ መለወጥ ጋር ተያይዞ የአካባቢ አየር ንብረት እየተዛባ በመምጣቱ የተለያዩ የእጽዋትና የእንስሳት ውጤቶችን አሁንም ከውጪ እያስመጣች ነው ብለዋል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ  ወጣት ተመራማሪዎችና ሣይንቲስቶች  በመተባበርና በቅንጅት የሚያከናውኗቸው የምርምር ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የላቀ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአገር ውስጥና በውጪ አገራት ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ጥምረትን በመፍጠር ዘርፈ ብዙ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

የአዲስ ኮንቲኔንታል አፍሪካ ሄልዝ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር የማነ ብርሃኔ የምርምር ልምዳቸውን መነሻ አድርገው እንደገለፁት ተመራማሪዎች የምርምር ክሂሎታቸውን በማዳበር፣ የምርምርን ገንዘብ ወረቀት ላይ ብቻ ከማዋል እንዲሁም የተሠሩ የምርምር ሥራዎችን መልሶ ከመሥራት ይልቅ የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ አዳዲስ ጥናቶችን በማከናወን የአገሪቱን የልማት ግብ ለማሳካት ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

በደቡብ ክልል የጉጌ ተራራ የህዋ ሣይንስ ጥናትና ምርምር፣ ምግብን በአግባቡ የመያዝ ልምድና ተያያዥ ጉዳዮች፣ በጨንቻ ወረዳ በበልግ ወቅት የገብስ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና አሰባሰብ፣ የጨቅላ ህፃናትን ሞት ሊያፋጥኑ የሚችሉ ጉዳዮች እንዲሁም በአዲስ አበባ የህዝብ ሆስፒታሎች በድንገተኛና መሰል የህክምና ክስተቶች ላይ ሐኪሞች የሚኖራቸው ጭንቀት በዓውደ ጥናቱ ከቀረቡ 36 ጥናታዊ ጽሑፎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ጥራት ያላቸው ተመራማሪዎች ቁጥር አናሳ መሆን፣ የምርምር በጀትን በአግባቡ አለመጠቀም፣ የምርምር ሥራ ወረቀት ላይ ብቻ የሚቀር አድርጎ መመልከት እንዲሁም የተመራማሪዎች የምርምር እውቀት ማነስ የዘርፉ ክፍተቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የየኮሌጆቹ ተመራማሪዎች፣ ከመቐለ፣ ጎንደር፣ ወልድያ፣ ጅማ፣ ዲላ እና ሌሎችም በአጠቃላይ ከ13 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ተመራማሪዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት