ለሁለት የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራን እውቅና ተሰጠ

በቀድሞ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምሩቃን አዘጋጅነት ለዶ/ር ሚፍታ አህመድና አቶ ንጉሱ በቀለ የእውቅና አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት መጋቢት 13/2011 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡
መምህራኑ በማስተማር ቆይታቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ፣ ለተማሪዎቻቸው ባካፈሉት እውቀትና ባሳዩት መልካም ባህርያት ለሌሎች መምህራን መነቃቃትን ለመፍጠር የእውቅና አሰጣጥ ፕሮግራሙ ተዘጋጅቷል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ መምህር ለሚያከናውናቸው ተግባራት የመጀመሪያው ምስክር ተማሪው ነውና መምህራኑ ለተማሪዎቻቸው ያሳዩት መልካም ተግባር በተማሪዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ ይህን በጎ ሥራ  ሌሎችም ተጋርተው አርአያነታቸውን ሊከተሉ ይገባልም ብለዋል፡፡

ልምድ ያላቸውንና ትጉህ መምህራንን ተሞክሮ ለማጋራት ቀደም ሲል የተዘጋጀውን መድረክ ለማጠናከርና ሌሎች መምህራን መልካም ተሞክሮን እንዲቀስሙ ለማነሳሳት ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ ተናግረዋል፡፡

ተሸላሚ መምራኑ ይህ በእነርሱ ጥረት ብቻ እንዳልተገኘ ጠቁመው የተማሪዎችን ውጤት ሊቀይሩ ይችላሉ ብለው ያመኑትን ከሌሎች የትምህርት ክፍሎች ጋር  አብረው መሥራታቸው ለስኬት እንዳበቃቸው ጠቅሰዋል፡፡ ተማሪዎች ከስኬት እንዲደርሱ የሁልጊዜ ሀሳባችን በመሆኑ ማድረግ ያለብንን ለማድረግ ችለናል ያሉት መምህራኑ ይህን ተግባራችንን በመመልከት እውቅና ለሰጡን አካላት ከልብ የመነጨ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የመማሪያ ክፍሎች እጥረትና ሌሎችም የመማር ማስተማሩን ሥራ የሚያግዙ ግብዓቶች አለመሟላት ለሥራቸው እንቅፋት እንደነበሩ ተናግረው በአሁኑ ወቅት ችግሮቹ ሙሉ በሙሉ ተቀርፈው ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ተማሪዎችን ከወቅቱ ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰርና የመማር ማስተማሩን ሥራ አጠናክረን በመቀጠል ዩኒቨርሲቲውንና አገራችን ኢትዮጵያን ወደተሻለ የእድገት ምዕራፍ ለማምጣት ቁርጠኛ ነን ብለዋል፡፡

የአዲስ ገቢ ተማሪዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በየጊዜው ተከታትሎ ማጥራትና መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባውም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በዕለቱ ከቀድሞው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምሩቃን የተዘጋጀ ልዩ ስጦታ ለ2ቱ መምህራን ተበርክቷል፡፡

በእውቅና አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን፣ የ2ቱ ኢንስቲትዩቶች የተማሪ ተወካዮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት