የዩኒቨርሲቲው የህግ ት/ቤት በጅንካ ከተማ ለሚገኙ የማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ስልጠና ሰጠ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ህግ ት/ቤት በጅንካ ከተማ ለሚገኙ የቀበሌ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ከመጋቢት 27-28/2011 ዓ.ም በሰብዓዊ መብቶች፣ በቤተሰብ ህጎች፣ በውርስ ህግ፣ በደ/ብ/ብ/ህ/ክ መንግሥት ፍርድ ቤቶች አደረጃጀትና ማኅበራዊ ፍ/ቤቶች ላይ ያተኮረ ስልጠና ሰጥቷል፡፡  ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ
የስልጠናው ዓላማ የህግ ምክር አገልግሎት እና መረጃ ከፍለው ማግኘት ለማይችሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለመብታቸው መረጃ በማግኘት ህጋዊ መብቶቻቸውን በተገቢው መንገድ እንዲጠይቁና  እንዲጠቀሙ ማስቻል፣ አገልግሎት ጠያቂዎች መብቶቻቸውን ለማስከበር የሚያስችላቸውን ክሂሎት ማዳባር እንደሆነ የሕግ ት/ቤት ዲን አቶ ደርሶልኝ የኔአባት ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ደርሶልኝ ገለፃ የማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች በፍትህ ሥርዓት ውስጥ አስተዋፅኦ ያላቸው ሲሆኑ ተቋሙ በቀበሌ ደረጃ በማኅበረሰቡ መካከል የተለያዩ ግጭቶች ሲፈጠሩ ፍትህ የሚሰጥ ነው፡፡ የቀበሌ ፍርድ ቤት አርሶ አደር፣ ነጋዴ እና አልፎ አልፎ ጡረተኞችና የመንግሥት ሠራተኞች በዳኝነት የሚሳተፉበት በመሆኑ የሕግ ዕውቀታቸው አነስተኛ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ የቀበሌ ፍርድ ቤት ዳኞች ፍትህን ሲያዛቡ ይስተዋላል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍና የተሻለ የህግ ዕውቀትና ግንዛቤ ኖሯቸው የፍትህ ሥርዓቱን እንዲያግዙ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ስልጠናዎችን ይሰጣል፡፡
በስልጠናው እንደተብራራው በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 10 መሠረት ሰብአዊ መብቶች የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ በተፈጥሮ ያገኛቸው መብቶች ናቸው፡፡ የሐብት መጠን፣ የኃይማኖት፣ የዘር ፣የቀለም፣ የፆታና የመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይደረግ ለሰው ልጅ በሙሉ በእኩልነት ሊከበሩለት የሚገቡ መብቶች ናቸው፡፡
በውርስ ህግ ላይ ስልጠና የሰጡት አቶ እንየው ደረሰ በህጉ ውርስ ለማን ይሰጣል፣ ከውርሱ ማን ይነቀላል፣ ውርስ በስንት ዓይነት መልኩ ሊተላለፍ ይችላል የሚሉና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ዳስሰዋል፡፡
አቶ ዳኛቸው ወርቁ በበኩላቸው የቤተሰብ ህግ የፍትሐብሔር ህግ አንድ ክፍል መሆኑንና በውስጡም ስለመተጫጨት፣ ጋብቻ፣ የጋብቻ ውጤቶች፣ የጋብቻ መፍረስና ውጤቶቹ እና ስለመውለድና የመወለድ ውጤቶች የሚያትት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ሰልጣኞች ባሻ ፀጋዬ ታደሰና ወ/ሮ ዝናሽ ስዩም በሰጡት አስተያየት በማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኝነታቸው የፍትሀብሔርና የወንጀል ጉዳዮችን እንደማይሠሩ ገልጸው ማኅበራዊ ችግሮችን እንድንፈታና ባለጉዳዮች እንዳይጉላሉ ስልጠናው ትልቅ ግብዓት ይሆነናል ብለዋል፡፡ ስለ ቤተሰብ እና የውርስ ህግ የማያውቋቸውን ጽንሰ ሀሣቦች መረዳት መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚጠዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት