የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሣይንስ ትምህርት ቤት ከትምህርት ቤቱ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ለተወጣጡ ለርዕሳነ መ/ራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እና የትምህርት ጽ/ቤት ባለሙያዎች በስትራቴጂክ ዕቅድ /SP/ ዝግጅትና ትግበራ እንዲሁም በትምህርት ቤት ማሻሻያ ፕሮግራም /SIP/ ላይ ያተኮረ ስልጠና ከግንቦት 26-28/2011 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡

የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሣይንስ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንደገለጹት የትምህርት ቤት ማሻሻያ ፕሮግራም ስልጠና ከ2004 ዓ/ም ጀምሮ ባለመሰጠቱ በስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅትና ትግበራ ላይ ከፍተኛ የክህሎት ክፍተት አስከትሏል፡፡ ክፍተቱን ለመቅረፍ ስልጠና ወስደው ወደ ተግባር ሊቀይሩና ከ2012 ዓ/ም ጀምሮ ለ3 ዓመት የሚያቅዱት እቅድ የተሟላና የተማሪ ውጤት መሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ሰልጣኞች ሌሎች ሰነዶችን በማንበብ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት በማጎልበት በቀጥታ ወደ እቅድ ዝግጅትና ትግበራው እንዲገቡ አሳስበው የወረዳ ጽ/ቤት ኃላፊዎችም ርዕሳነ መ/ራኑ ማቀድ አለማቀዳቸውን ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት በዳይሬክቶሬቱ አማካይነት በትምህርት ቤቶች ላይ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን ለአርባ ምንጭ፣ ለሳውላ እና ለዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ 2ኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች 2.1 ሚልየን ብር የሚያወጡ የላቦራቶሪ እቃዎች በመገዛት ላይ ናቸው፡፡ ት/ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች የፀሐይ ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን፣ የተለያዩ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ መሠራቱንና የተለያዩ ስልጠናዎች የተሰጡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ቤት የ3 ዓመት እስትራቴጂክ ዕቅድ/SP/ እና በትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም /SIP/ ላይ ያተኮረ ስልጠና የሰጡት የሥነ-ትምህርት ት/ክፍል ኃላፊ መ/ር ሰለሞን ሳጶ ስልታዊ ዕቅድ የት መድረስ እንደምንፈልግ አልመን የምናስቀምጥበት ከመሆኑም ባሻገር ሥራዎችን በተቀላጠፈ አኳኋን ማከናወን እንዲቻል የሚያደርግ ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም SIP ማለት በአጠቃላይ ት/ቤቶች ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ ከተለያዩ የትምህርት ቤት ርዕሰ ጉዳዮች አንፃር በመዳሰስና ግለ ግምገማ በማካሄድ የትምህርት ሂደቱንና ግብዓቶቹን  በማሻሻል ተማሪዎች የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያስችል ሂደት ላይ  ያተኮረ ፅንሰ ሀሳብ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አሰልጣኙ ገለፃ የት/ቤት ማሻሻያ ዋነኛ ትኩረቱ በተማሪዎች መማርና የመማር ውጤት ላይ ሲሆን ለዚህ ስኬት ትምህርት ቤቶች በቅድሚያ ደካማና ጠንካራ ጎናቸውን በመለየት ከእያንዳንዱ ት/ቤት አበይት ርዕሰ ጉዳይ አንፃር ቅድመ ትኩረት በማድረግና ግብ በመጣል ሁሉም የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ አባላትና ባለድርሻ አካላት ለተማሪዎች ውጤት ከፍተኛ በሆነ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በዕቅድ ባህሪያት፣ ዕቅድ ለማቀድ በሚያስፈልጉ ነገሮች፣ በትምህርት ቤት መሻሻል መርሃ ግብር፣ በትምህርት ቤት ዓበይትና ንዑሳን ርዕሰ ጉዳዮች፣ በትምህርት ቤት መሻሻል አስፈላጊነት፣ ደረጃዎች፣ እንዲሁም በትምህርት ቤት መሻሻል እቅድ ዝግጅት መሪ መርሆዎችና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ሰፊ ገለፃ አድርገዋል፡፡

የዕቅድ አዘገጃጀትን ጥራት በማምጣት በትምህርት ቤቶች ላይ ጥሩ የሆነ የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የገለፁት የትምህርት ቤቱ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ር ይሁንሰላም አስራት በትምህርት ተቋማት ውስጥ እየተስተዋሉ ያሉ ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ በርካታ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ርዕሳነ መ/ራን ራሳቸውን ችለው የተቋማቸውን እቅድ የሚያዘጋጁበት አቅም እንዲፈጥሩ ብሎም ያገኙትን ዕውቀት መሠረት በማድረግ የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማሳተፍ ትክክለኛ የሆነ ዕቅድ ማቀድ እንዲችሉ እንደሚያደርግ ገልፀው ዕቅዳቸውን በመገምገም ት/ቤቶቹን ካሉበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉ/ም ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ እንደገለፁት ለትምህርት ጥራት ትኩረት ከመስጠት አኳያ የአመራሩን አቅም መገንባት ጉልህ ሚና አለው፡፡ ስልጠናው ለለፉት 7 ዓመታት ሳይሰጥ በመቆየቱ የሚታየውን የተነሳሽነት ክፍተት በመሙላት አቅም ለመገንባት የሚረዳ እና በሣይንሳዊ የዕቅድ አዘገጃጀት ዘዴ በመታገዝ የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖር የሚያስችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው አፈፃፀሙ ላይም  ክትትል በማድረግ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተጨማሪ ድጋፍ እየሰጠ የሚገመግም ይሆናል ብለዋል፡፡

ዶ/ር የቻለ አክለውም በቀጣይ የሚቀርቡ የስልጠና ፍላጎቶችን መሠረት በማድረግ ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ውጪ ለሚገኙ ሌሎች የጋሞና የጎፋ ዞን ወረዳ  ት/ቤቶች የትምህርት አመራር አካላት ዩኒቨርሲቲው ስልጠና ለመስጠት ዝግጁ ስለሆነ ስልጠናው የሚሰጥበትን ጊዜና ሌሎች ግብዓቶችን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ሰልጣኞች የወሰዱትን ስልጠና ለሌሎች በስልጠናው ላልተሳተፉ የትምህርት ባለሙያዎች በሚገባ ማስተላለፍ እንዳለባቸው አሳስበው የትምህርት ቤቱ ዲን፣ መ/ራንና የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ  የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እያከናወኑ ላሉት ተግባርና የሞራል ተነሳሽነት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡