በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ በሒሳብ ትምህርት አዘጋጅነት ‹‹ሒሳብ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት›› የተሰኘ ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ከግንቦት 23-24/2011 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡
የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ሒሳብ የሳይንሱ መስክ መግቢያ ቁልፍ እንደሆነ ገልፀው በዚህ የምርምር ኮንፍረንስም በሀገሪቱ ያሉ የዘርፉ ምሁራን የሚሳተፉበትና የምርምር ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት በመሆኑ በዩኒቨርሲቲያችን ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ የ2ኛና 3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች የምርምር ልምድ እንዲያገኙ በማድረግ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

የምርምርና ማህበረሰብ አገ/ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ አሁን ላይ በዓለማችን የሚታዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች መሠረታቸው ሒሳብ እንደሆነ ገልፀው መስኩ በሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥም ቢሆን የጎላ ሚና የሚጫወት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የዛሬው የምርምር ኮንፍረንስ በዩኒቨርሲቲው ሲደረግ የመጀመሪያ መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር ተክሉ በዋናነት በመስኩ መምህራንና ተመራማሪዎች መካከል የልምድ ልውውጥና በመስኩ በተገኙ የምርምር ውጤቶችና አዳዲስ ፈጠራዎች ላይ ውይይት እንዲያደርጉ ያግዛል ብለዋል፡፡

የምርምር ኮንፍረንሱ በሒሳብ ትምህርት መስክ የተሰሩ ምርምሮችን በማቅረብ በዘርፉ ምሁራን በማስተቸትና ውይይቶችን በማድረግ የልምድ ልውውጥ አንዲኖር እንዲሁም ለማስተርስና ፒ. ኤች .ዲ ተማሪዎቻችን የምርምር ልምድ እንዲያገኙ ለማስቻል እንደተዘጋጀ የሒሳብ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ስምዖን ደርኬ ገልፀዋል፡፡

ከኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች መካከል የOPERATION RESEARCH የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት አቶ ስሜነህ ሁናቸው በዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ በዘርፉ እየተሰሩ ያሉ ወቅታዊ የጥናትና ምርምር ውጤቶች የቀረቡበት በመሆኑ እንዲሁም በሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ የዘርፉ ምሁራን ተገኝተው የምርምር ሥራዎቻቸውንና ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ በመደረጉ አንደሳቸው ላሉ ተማሪዎች ትልቅ ጥቅም እንዳለው ገልፀው አሳቸውም በኮንፍረንሱ አዳዲስ ልምዶችን ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

በኮንፍረንሱ 2 የአንኳር ሀሳብ ንግግሮችና 16 የምርምር ሥራዎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ የዘርፉ ምሁራን ተሳተፈዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት