ዩኒቨርሲቲው በ‹‹STEM›› ፕሮጀክት ከጋሞ፣ ጎፋ፣ ሰገን፣ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ለተወጣጡ 320 ተማሪዎች የሣይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሣብ ትምህርት መስኮች ለአንድ ወር ሲሰጥ የነበረው የተግባር ሥልጠና ተጠናቋል፡፡ ነሐሴ 13/2011 ዓ/ም ከሠልጣኞቹ ጋር የማጠቃለያ ውይይትም ተደርጓል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ
የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ሥልጠናው በዋናነት ተማሪዎች ሥልጠናውን በሚወስዷቸው የትምህርት መስኮች በየትምህርት ቤቶቻቸው የሚያገኙት የተግባር ትምህርት ውስን በመሆኑ ዓመቱን በሙሉ በቲዎሪ ደረጃ የተማሩትን በተግባር ለማጠናከርና ለማስጨበጥ የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በፕሮጀክቱ አማካይነት ከ2008 ጀምሮ በአካባቢው ከሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ በትምህርታቸው የተሻለ አፈፃፀም ላላቸው ተማሪዎች ሥልጠናውን ሲሰጥ መቆየቱን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ  ከጊዜ ወደ ጊዜ የሠልጣኞች ቁጥርም ሆነ የሥልጠናው አሰጣጥ ሂደት ዕድገት እያሳየ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በማጠቃለያ ውይይቱ ወቅት በተማሪዎቹ እንደ ችግር የተነሱ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራ የተናገሩት ዶ/ር ተክሉ የ‹‹STEM›› ፕሮጀክትን ወደ ማዕከልነት ለማሳደግ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡ ማዕከሉ ሲቋቋም ሥልጠናው በክረምት ብቻ ሳይወሰን በጋውን ጭምር ተማሪዎቹ የፈጠራ ሥራ የሚያከናውኑበት ማዕከል ይሆናል ብለዋል፡፡
ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በአ/ምንጭ ከተማ የጫሞ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ተማሪ ፍፁም ፋንታ በበኩሏ ዩኒቨርሲቲው በትምህርታቸው የተሻለ አፈፃፀም ያላቸውን ተማሪዎች ከተለያዩ አካባቢዎች በማምጣት ሥልጠና በመስጠቱና የዕረፍት ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረጉ አበረታችና የሚያስመሰግን ተግባር ነው ብላለች፡፡ ተማሪዋ  ሥልጠናው በጥሩ ሁኔታ እንደተሰጠ ገልፃ ነገር ግን 10ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ስለሆኑ ለፈተናው በሚያዘጋጁ ጉዳዮች ላይ ሥልጠናው ትኩረት ቢያደርግና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርትም በሥልጠናው ቢካተት የሚል ሀሳብ ሰጥታለች፡፡
ከኮንሶ ዞን የመጣው የ9ኛ ከፍል ተማሪ ሮቤል ጮርሳሞ በአንድ ወር የዩኒቨርሲቲ ቆይታው የተግባር ዕውቀት እንዳገኘ ገልጾ በዋናነት ሥልጠናው ተግባር ላይ ያተኮረ በመሆኑ ከዚህ ቀደም በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ ብቻ የሚያውቃቸውን በርካታ ጉዳዮች በተግባር ማየት በመቻሉ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በሥልጠናው ተማሪዎቹ በተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ ለ15 ቀናት የፊዚክስ፣ ኬሚስትሪና ባዮሎጂ የተግባር ትምህርት ያጠናቀቁ ሲሆን በቀጣይም በዋናው ግቢ የኢንጂነሪንግ፣ ኮምፕዩተርና ሒሳብ ትምህርት ዘርፎች የሚሰጠውን ሥልጠና ለ15 ቀናት ወስደዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት