ዩኒቨርሲቲው በ2012 የትምህርት ዘመን ሠላማዊ መማር ማስተማር ለማረጋገጥ በተዘጋጀ የሠላም ጥምር ግብረ ኃይል መሪ ዕቅድ ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ጋር ጳጉሜ 2/2011 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡click here to look the picture

ጥምር ግብረ ኃይሉ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በማዕከል እንዲሁም በየካምፓሱ የሚቋቋም ሲሆን ዓላማውም የትምህርት ዘመኑ በተሻለ ሁኔታ ውጤታማና ሠላመዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማድረግ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል፡፡ ጥምር ግብረ ኃይሉ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ባሻገር የተማሪዎች ኅብረት ተወካዮችን፣ የሠላም ፎረም አመራሮችን፣ የዞንና የከተማ የሥራ ኃላፊዎችንና ፀጥታ አካላትን ያካተተ መሆኑንም ፕሬዝደንቱ ገልፀዋል፡፡
ጥምር ግብረ ኃይሉ በዋናነት ከታች እሰከ ላይ ባለው የዩኒቨርሲቲው መዋቅር መማር ማስተማሩን ሊያውኩ የሚችሉ ጉዳዮችን በየጊዜው እየተከታተለና እየገመገመ መፍትሔና ማስተካከያ የሚሰጥ መሆኑን ዶ/ር ዳምጠው ገልፀዋል፡፡ ጥምር ግብረ ኃይሉ በውስጥና በውጪ ጭምር የሚዋቀር መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ መዋቅሩ ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ ይሠራል ብለዋል፡፡
በትምህርት ዘመኑ ለተማሪዎች ቅበላ ይረዳ ዘንድ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እቀድ ተዘጋጅቶ እየተሠራ ሲሆን በቅርቡም አፈፃፀሙን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ልዑክ ወደየ ካምፓሱ በመሄድ ምልከታ እንደሚያደርግና ሥራው ያለበትን ደረጃ በመገምገም አቅጣጫ እንደሚሰጥ ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል፡፡
ሠላማዊ የመማር ማስተማሩ ሥራ ካለ ህብረተሰቡ ተሳትፎ ስኬታማ መሆን ስለማይችል መስከረም መጀመሪያ አካባቢ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሐይማኖት አባቶችና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት