የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የ2011 ማጠቃለያና የ2012 የትምህርት ዘመን መባቻን ምክንያት በማድረግ ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቁሳቁሶችን እንዲሁም ጧሪ ለሌላቸው አቅመ ደካማ አረጋዊያን የተሠሩና የታደሱ ቤቶችን የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በተገኙበት ጳጉሜ 5/2011 ዓ.ም አስረክቧል፡፡በፕሮግራሙ ዩኒቨርሲቲው በሻራ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ያስገነባቸው የመማሪያ ክፍሎችም ተመርቀዋል፡፡  ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው ለአገሪቱ ልማትና እድገት የተማረ የሰው ኃይል ከማፍራት ባሻገር ዘርፈ ብዙ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመደበኛ ፕሮግራም የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ላላገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የትምህርት ዕድል፣ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ለ1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች መምህራን የአጭርና የረጅም ጊዜ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እንዲሁም ለትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎች ግባታና የቁሳቁስ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለፁት በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በክረምቱ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ተመራቂ ተማሪዎችንና የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞችን በማስተባበር 133 ዩኒት ደም መሰብሰቡ፣ የ2 አቅመ ደካማ አረጋዊያን መኖሪያ ቤቶች መጠገናቸው፣ በሐምሌ 22ቱ የአረንጓዴ አሻራ ቀን ከ20 ሺ በላይ ችግኞች መተከላቸው፣ ለአርባ ምንጭ፣ ሳውላና ኮሚዩኒቲ 2ኛ ደረጃና መሠናዶ ት/ቤቶች 1.5 ሚለዮን  ብር በላይ ወጪ በማድረግ የቤተ-ሙከራ  ቁሳቁስ ግዥ መፈጸሙ፣ ለሰባት የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የማጣቀሻ መፅሐፍት ተገዝተው መበርከታቸው፣ ለአርባ ምንጭ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት የ216 ወንበርና ጠረጴዛ እና የ15 ጥቁር ሠሌዳ ድጋፍ መደረጉ፣ ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስና የአልባሳት ድጋፍ መደረጉ እንዲሁም ከዞንና ከከተማ ተቋማት ለተወጣጡ 1,300 ሠራተኞች የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሥልጠና መሰጠቱ ይጠቀሳሉ፡፡

የም/ማ/አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከተመሠረተ ጀምሮ በዓይነትና በመጠኑ እየበዛና እየሰፋ የሚሄድ የማኅበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተናግረው ከዘርፉ ሥራዎች ውስጥ ወደ ማኅበረሰቡ የተሸጋገሩና ተጠቃሚነትን ያረጋገጡም አሉ ብለዋል፡፡ 

ጦሎላ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ዶርዜ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ጫኖ ዶርጋ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ አርባ ምንጭ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ በጎፋ ዞን ጋዳ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እና የላንቴ ቀበሌ ደጉ ሳምራዊ የወጣቶች ማዕከል የማጣቀሻ መፅሐፍትና የመማሪያ ቁሳቁሶች ተበርክተውላቸዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት