አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ለተወጣጡ ከ570 በላይ መምህራን፣ ርዕሳነ መ/ራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና የትምህርት ባለሙያዎች ከመስከረም 5-9/2012 ዓ/ም  ለ5 ተከታታይ ቀናት የቆየ የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ሥልጠናው በቅድመ መደበኛ ትምህርት፣ በተከታታይ የሙያ ማሻሻያ፣ በልዩ ፍላጎት ትምህርት እንዲሁም ጋሞኛ ቋንቋ ማስተማር ዙሪያ ያተኮረ ነው፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው በሥልጠናው የተከታቱ ርዕሰ ጉዳዮች የ2012 የትምህርት ዘመን ከመጀመሩ አስቀድሞ ሥልጠና ያስፈልግባቸዋል ተብለው በዞኑ ት/መምሪያ የተለዩ ዘርፎች ናቸው፡፡ ሥልጠናው በዞኑ በሁሉም የትምህርት እርከኖች የሚሰጠው ትምህርት ውጤታማ እንዲሆን የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ በመታመኑ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ በጀት በመመደብ ሥልጠናውን ለመስጠት ሁኔታዎችን አመቻችቷል ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ እንቁ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲው መደበኛ ተማሪዎችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት እያደረገ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የሰው ኃይል ላይ የሚሠራው ሥራ ለአገር ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያበረክተውን ሚና በመገንዘብ በተጣበበ ጊዜ ውስጥ ሰፊ ሥልጠና በመስጠቱ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለፃ ሥልጠናው የ2012 የትምህርት ዘመን በዞኑ የተሳለጠና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የመምህራንን ግንዛቤ በማጎልበትና በማነቃቃት ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

በሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህርይ ሣይንስ ት/ቤት የሥነ-ልቦና መምህር የሆኑት አቶ ይሁንሰላም አሥራት በበኩላቸው ሥልጠናው የተሰጠባቸው አራቱ ርዕሰ ጉዳዮች በጋሞ ዞን በአጠቃላይ ትምህርት መስክ እንደ ክፍተት የሚታዩ በመሆናቸው የዕውቀት፣ የክህሎትና የአመለካከት ክፍተቶችን በመቅረፍ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል፡፡ ሥልጠናው የአሰልጣኞች ሥልጠና እንደመሆኑ በቀጣይ ወደ ታች ወርዶ ለሁሉም መምህራን መሰጠት እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

ከአ/ምንጭ ከተማ የመጡት ሠልጣኝና የልዩ ፍላጎት መምህርት ወ/ሮ የትምወርቅ ነጋሽ በሥልጠናው ለሥራቸው አጋዥ የሆኑ አዳዲስ ግንዛቤዎችን እንዳገኙ ገልፀው በተለይ በልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት መስክ እስከ ትምህርት ቤት የሚወርድ ወጥ የሆነ አሠራር ቢዘረጋ እንዲሁም  የምልክት ቋንቋ ሥልጠና በየትምህርት ቤቱ የሚሰጥበት ሁኔታ ቢመቻች ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ አፀደ ሕፃናት ት/ቤት ርዕሰ መምህርት ወ/ሪት ሣራ ጎይዳ በበኩላቸው በሥልጠናው በሕፃናት አያያዝ፣ እንክብካቤ፣ መብቶች እንዲሁም የማስተማሪያ ስልቶች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ገልፀው ያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ለማጋራት እንደተዘጋጁ ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናው ከአዲስ አበባና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች በተወጣጡ የዘርፉ ምሁራን የተሰጠ ሲሆን በቀጣይም ለሁሉም መምህራን በክላስተር ደረጃ የሚሰጥ ይሆናል፡፡