አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአዲሱ ዓመት የመማር ማስተማር ሂደትን ሠላማዊና ምቹ ለማድረግ የጀመረውን አደረጃጀት አጠናክሮ በመቀጠል  አርባ ምንጭ ከተማ  የተረጋጋች፣ የሠላምና ምቹ የሥራ ቀጠና እንድትሆን እንደሚሠራ ገልጿል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የ2011 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምና የአዲሱ ዓመት በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው የተረጋጋ ሠላምና ጸጥታን ለማስፈን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር መስከረም 08/2012 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ በ2011 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው የነበረው የመማር ማስተማር መልካም ገጽታዎች እንዲሁም እንደ አገር የተስተዋሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ምን እንደሚመስሉ በውይይቱ ተነስተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አዲሱ ዓመት እንደ ቀድሞው ሁሉ በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ሠላማዊና የተሻለ የትምህርትና የሥራ ዘመን ሆኖ እንዲጠናቀቅ ልዩ ትኩረትን በሚሹ ጉዳዮችና በጋራ መሠራት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ውይይቱ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ፕሬዝደንቱ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው በሰው ኃይል፣ በምርምርና በማኅበረሰብ አገልግሎት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እና በዩኒቨርሲቲውም ሆነ ከዩኒቨርሲቲው ውጪ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር በመሆን ለመፍታት በተጠናከረ ሁኔታ እየሠራ ነው፡፡ በመሥሪያ ቤቶች የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት የአገልግሎት አሰጣጣቸውን አሳድገው ማኅበረሰቡን በቅልጥፍና እንዲያገለግሉ ዩኒቨርሲቲው ለዞኖችና ለአካባቢ አስተዳደር አካላት በመጀመሪያ፣ በ2ኛና በ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ማመቻቸቱንም ተናግረዋል፡፡

በአዲሱ ዓመት በሚጀምረው አዲሱ የትምህርት ሥርዓት መሠረት አዲስና ነባር ተማሪዎች ከወላጆቻቸውና በአካባቢያቸው ከሚገኙ ወረዳዎች ጋር  ውል ተፈራርመው የሚያመጡት የማረጋገጫ ወረቀት ከፋይላቸው ጋር እንዲቀመጥ መደረጉ በዩኒቨርሲቲው በሚኖራቸው ቆይታ በንብረት አያያዝና ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ የነጭ ሳር ክ/ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በላይ ዳሮታ ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢው አስተዳደር ጋር ተናቦና ተቀናጅቶ ቢሠራ ችግሮችን ማስተካከል እንደሚቻል ገልፀው በሚሠሩበት ክ/ከተማ ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጥምረት የሚሠሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

የመሃል ከተማ ክ/ከተማ ነዋሪ አቶ ካንቲያ አካኮ በበኩላቸው በአርባ ምንጭ ከተማ ሠላምና ጸጥታ እንዲሰፍን እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ተማሪው በሠላማዊ መንገድ ተረጋግቶ መማር እንዲችል የከተማው መስተዳደርና የአካባቢው ማኅበረሰብ የተቆራኙ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ በዚህ መልኩ ከተሠራ የንብረት መጥፋትንና ስርቆትን በመቀነስ የተቋሙንና የአካባቢውን ገጽታ በጋራ ለመገንባትም እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ከጸጥታና ደኅንነት እና ሌሎች ዘርፎች የተወጣጡ ተሳታፊዎች የውይይቱ ታዳሚዎች ናቸው፡፡