ዩኒቨርሲቲው አርባ ምንጭ ከተማ ከሚገኙ ተስፋ ጎህ፣ አዲስ ተስፋ፣ የኤች አይ ቪ ንቅናቄ እና ቤተ-ሳይዳ የኤ ች አይ ቪ/ኤድስ ማኅበራት ለተመለመሉ 120 ህፃናትና ታዳጊዎች መስከረም 08/2012 ዓ/ም የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድጋፍ ከተደረገላቸው 120 ህጻናት መካከል 94ቱ የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝና በበሽታው ወላጆቻቸውን  ያጡ በመሆናቸው የጥምር ችግሮች ተጋላጭ እንዳደረጋቸው ተገልጿል፡፡ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ መኩሪያ እንደገለጹት በዋናነት የኤች አይ ቪ/ ኤድስና የስነ-ተዋልዶ የጤና ችግሮችን መከላከል የዳይሬክቶሬቱ ቀዳሚ ተግባር ሲሆን በ2012 የበጀት ዓመት ከታቀዱ ተግባራት መካከል በተለይ ወላጅ አጥና የኤች አይ ቪ/ኤድስ ተጠቂ የሆኑ ልጆችን መደገፍ ነው፡፡ መሰል የጤና ችግር ውስጥ ያሉ ህጻናትን መደገፍ በራሱ በሽታውን ከመከላከያ መንገዶች አንዱ በመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚያሻውና ወደ ፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በበሽታው የተጠቁና ወላጅ የሌላቸው ልጆች በመሰል ተግባራት ስነ-ልቦናቸው ካልታደሰ፣ በአግባቡ ካልተያዙ እና ድጋፍና ክትትል ካልተደረገላቸው ለትምህርት ያላቸው ቦታ መቀነስ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ለጎዳና ህይወት መጋለጥ ብሎም ወደ ሱሰኝነትና ያልተፈለጉ ሥራዎች መግባትን ሊያስከትል እንደሚችል አቶ መርክነህ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የበሽታው ተጠቂዎች መገለልና መድልኦ የሚደርስባቸው ከሆነና በአግባቡ እንክብካቤ ካልተደረገላቸው መራራ ህይወት እንዲገፉ ከማድረጉ ባሻገር የበቀለኝነት ስሜት ተፈጥሮባቸው ለወንጀል እንደሚጋበዙና ሌሎች ለአገር አስጊ ወደ ሆኑ ነገሮች የሚያስገባቸው መሆኑን አቶ መርክነህ  አስረድተዋል፡፡

ከተስፋ ጎህ ማኅበር የመጣችው መዲና እንድሪስ በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰቷን ገልጻ ከትምህርት ቁሳቁስ በተጨማሪ ሌሎችም ድጋፎች በዘላቂነት መቀጠል እንዳለባቸውና በተለይ 10ኛና 12ኛ ክፍልን አጠናቀው ውጤት ያልመጣላቸውና መሰል ችግር ያለባቸው ሌሎች ልጆችም በድጋፉ የሚካተቱበት ሁኔታ ቢፈጠር መልካም መሆኑን ተናግራለች፡፡

በተመሳሳይም በተስፋ ጎህ ማኅበር ውስጥ የድርሻውን እየተወጣ ያለው ወጣት ኡመር እንድሪስ በድጋፉ መደሰቱን ጠቅሶ ዩኒቨርሲቲው በኤች አይ ቪና በሌሎች የስነ-ተዋልዶ ጤና ዙሪያ የሚሰጣቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት