የግንባታ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት ለማጠናቀቅና የዩኒቨርሲቲውን የገቢ አማራጮች ለማስፋትና ለማሳደግ እየተሠራ ነው

በ2012 በጀት ዓመት በዩኒቨርሲቲው በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ገለፀ፡፡ የኢንተርፕራይዞችን መዋቅርና አሠራር በመቀየርና ሌሎች አዳዲስ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን በመቀየስ 47 ሚሊየን ብር ገቢ ለዩኒቨርሲቲው ለማስገኘት እንዳቀደም ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው በሚገኙ 3 ኢንተርፕራይዞች ከዚህ ቀደም ሲስተዋሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር፣ የፋይናንስና የንብረት አያያዝ ችግሮች እንዲቀረፉ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም ኢንተርፕራይዞቹ ኦዲት ተደርገው አለማወቃቸው የቅሬታ ምንጭ እንደነበር የተናገሩት ወ/ሮ ታሪኳ አሁን ላይ የኢንተርፕራይዞቹ ከ2009-2010 ዓ/ም አፈፃፀም ኦዲት ተደርጓል፡፡

ኢንተርፕራይዞቹ የተለያዩ ስያሜዎችን ይዘው 3 መሆናቸው እንዲሁም ከዚህ ቀደም የነበረው መመሪያ እምብዛም ጠቃሚ እንዳልሆነ በዳሰሳ ጥናት በመታወቁ አዲስ የኢንተርፕራይዝ ማሻሻያ መዋቅር መመሪያ ተዘጋጅቶ የተለያዩ ደረጃዎችን አልፏል፡፡ መዋቅሩ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ በተቀመጠ አቅጣጫ መሠረት በሕግ ባለሙያዎች ታይቶ አስተያየት የተሰጠበት በመሆኑ በቅርቡ ጸድቆ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በመመሪያው መሠረት ሦስቱ ኢንተርፕራይዞች ወደ አንድ በመምጣት በውስጡ የተለያዩ ቅርንጫፎች ያሉት ሆኖ ‹‹የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኢንተርፕራይዝ›› በመባል እንደሚዋቀር ወ/ሮ ታሪኳ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በነጭ ሳር ካምፓስ ቅጥር ግቢ እያስገነባ የሚገኘውን የነዳጅ ማደያ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ሥራ ለማስጀመር እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ም/ፕሬዝደንቷ ማደያው ተጨማሪ አገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች ያሉት በመሆኑ ሕንፃዎቹን በማከራየት ዩኒቨርሲቲው ገቢ እንደሚያገኝ ገልፀዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ ንግድ ቤቶች የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ፣ ግንባታው የተጠናቀቀውን የእንግዳ ማረፊያ ሥራ ለማስጀመርና በዩኒቨርሲቲው የሚገኘውን የመዋኛ ገንዳና የስፖርት ጂምናዚየሞች ለአገልግሎት ምቹ ለማድረግ የተለያዩ ቁሳቁሶች ግዥ በመፈጸም ከዘርፎቹ የሚገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግ ጽ/ቤታቸው በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ወ/ሮ ታሪኳ ተናግረዋል፡፡

ከግንባታ ፕሮጀክቶች ጋር ተያይዞ በዩኒቨርሲቲው በግንባታ ላይ የሚገኙ ነባር ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ም/ፕሬዝደንቷ የካፒታል በጀት እጥረት፣ የውጭ ምንዛሪ ችግርና የዋጋ ንረት የዘርፉ ተግዳሮቶች ቢሆኑም ችግሮቹን በመቋቋም ውጤታማ ለመሆን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ 2011 ዓ/ም እንደ አገር ከነበሩ ችግሮች ጋር በተያያዘ ዘርፉ ትልቅ ችግር ውስጥ የነበረ መሆኑን አስታውሰው በችግሮች ውስጥም ቢሆን የጨረስናቸው ፕሮጀክቶች ለስኬታማነታችን ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡ በቅርቡም የጫሞ ካምፓስ ቤተ-መጽሐፍትና የጂኦግራፊ ቤተ-ሙከራ እንዲሁም የአባያ ካምፓስ የመምህራን ቢሮ ሕንፃዎች እየተጠናቀቁ በመሆኑ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ርክክብ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ ትልልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ አንዱ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ ታሪኳ በ2012 በጀት ዓመት ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከዩኒቨርሲቲውና ከግንባታ አማካሪ ድርጅት ጋር የግንባታ ሂደቱን 90 በመቶ ለማድረስና በ2013 በከፊል ሥራ እንዲጀምር ጽ/ቤታቸው የሆስፒታሉን ዋና ግንባታና የሆስፒታሉን የፍሳሽ ማስወገጃ ጨምሮ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው 22 የሚሆኑ ነባርና አዲስ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ የሚገኙ ሲሆን በ2012 በጀት ዓመት ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ 450 ሚሊየን ብር ተመድቧል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት