በዩኒቨርሲቲው አዲስ ለተመደቡ ሴት ተማሪዎች የህይወት ክህሎት ስልጠና ተሰጠ

የዩኒቨርሲቲዉ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት በሁሉም ካምፓስ ለሚገኙ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች ከጥቅምት 15 -23/2012 ዓ/ም ባሉት የዕረፍት ቀናት የህይወት ክህሎት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

 

ስልጠናው ከሥነ-ባህርይ እና ከማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ክፍሎች በተወጣጡ በጎ ፈቃደኛ መምህራን የተሰጠ ሲሆን የማስታወሻ አያያዝ፣ የአጠናን ዘዴ፣ የጊዜ አጠቃቀም እንዲሁም ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲው አዲስ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ሊገጥሟቸው የሚችሉ ጉዳዮችን አካቷል፡፡

የዳሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ እንደገለጹት ሴት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ተግዳሮቶችን ቀድመው እንዲያውቁ፣ የጊዜ አጠቃቀምና የአጠናን ዘዴያቸውን እንዲያስተካክሉ፣ በራስ መተማመንን እንዲያጎለብቱ፣ በፈተና ጊዜ ከሚያጋጥም ጭንቀት ራሳቸውን አንዲከላከሉ እንዲሁም ከኤች አይ ቪ/ኤድስና ከሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮች ተጠብቀው በትምህርታቸው ብቁ ሆነው እንዲወጡ ለማስቻል ስልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡

የሥነ-ባህርይ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ማርቆስ ካንኮ በበኩላቸው ተማሪዎች የሌሎችን ፍላጎት በማይጎዳ መልኩ በይሉኝታ ሳይጠቁ ሀሳባቸውን፣ ስሜታቸውን፣ መብታቸውንና ፍላጎታቸውን እንዲገልጹና አገላለጻቸውም ምክንያታዊና እውነተኛ እንዲሆን ስልጠናው ክህሎት የሚያስጨብጥ ነው ብለዋል፡፡

ከሰልጣኝ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ፋንቱ ተሰማ ስልጠናው ከሰው ጋር እንዴት ተግባብቶ መኖር እንደሚቻል ግንዛቤ እንዳስጨበጣት ተናግራለች፡፡