አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ ዓለም አቀፍ የውኃ አመራር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የሰዎችን ፍልሰት አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር የፕሮጀክት ማስተዋወቂያና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ጥቅምት 25/2012 ዓ/ም በኃይሌ ሪዞርት አዘጋጅቷል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ አገራችን ኢትዮጵያ ከፍልሰት ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮችን እያስተናገደች የምትገኝ እንደመሆኗ ፕሮጀክቱ ለፖሊሲ አውጪዎች ሃሳቦችን በመጠቆም ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

ከ ዓለም አቀፍ የውኃ አመራር ኢንስቲትዩት የመጡት ዶ/ር አለን ኒኮል እንደገለፁት የፕሮጀክቱ ዓላማ ከፍልሰት ጋር በተያያዘ ምርምሮችን ሠርተው ለውሳኔ ሰጪ አካላት ማስረጃዎችን በመስጠት የተሻሉ ውሳኔዎችን መሠረት አድርገው ፖሊሲዎች እንዲቀረፁ ማድረግ ነው፡፡ የግብርና ሥራን ስኬታማ ለማድረግ ውኃ በበቂ ሁኔታ ማግኘት ካልተቻለ ዋነኛው የፍልሰት መንስኤ እንደሚሆንና ፍልሰትና ግብርና የጠበቀ ቁርኝት እንዳላቸው ይበልጥ ለመረዳት ፕሮጀክቱ ተቀርጿል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ፍልሰትን በአሉታዊ ጎኑ ብቻ ሳይሆን በመልካም ጎኑ ጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል የሚቃኝ ከመሆኑም ባሻገር ስደተኛው ብቻ ሳይሆን ስደተኛው የወጣበት ማኅበረሰብና አካባቢ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖም የፕሮጀክቱ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ ዶ/ር መንግሥቱ ደሳለኝ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በአውሮፓ ኅብረት የሚደገፍና ፍልሰት ላይ የሚሠራ ትልቅ ፕሮጀክት ሲሆን በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከየካቲት 2019 እስከ ጥር 2022 ዓ/ም የሚቆይ ነው፡፡ የፍልሰት መጠኑ በዓለምና በአገር ደረጃ ምን እንደሚመስል በማነፃፀር ለማጥናት በአውሮፓ፣ በአፍሪካ እና በእስያ አህጉራት ላይ ይሠራል፡፡ በኢትዮጵያ የፕሮጀክቱ የሥራ አጋር ከሆኑት አርባ ምንጭ፣ መቐለ እና ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ጥናቶችን እንደሚያካሂዱም ገልፀዋል፡፡ የፍልሰት ምክንያቶችና እርስ በራሳቸው ያላቸው ግንኙነት እንዲሁም በገጠሩ አኗኗር ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖና መሰል ርዕሰ ጉዳዮችንም በስፋት ቃኝተዋል፡፡

የጋሞ ዞን አስተዳደር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ እሸቱ አልቶ በበኩላቸው ፍልሰት የላኪም ሆነ የተቀባይ አካባቢዎችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ምህዳር እየቀየረው ይገኛል ብለዋል፡፡ የፍልሰት መነሻው ጦርነት፣ ግጭት፣ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የሥራ ዕድል መጥበብ እና የሥራ ባህል መውረድ ሲሆኑ በእነዚህ ምክንያቶች በአገራችን ሥር የሰደዱ የማኅበራዊ ኑሮ ችግሮች የሚስተዋሉ በመሆናቸው ሰዎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ እንደሚፈልሱ ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ ፖሊሲዎች፣ አዋጆች፣ ህጎችና ደንቦች በአገራችን የወጡ ቢሆንም ፖሊሲው ከገጠር ወደ ከተማ በፍጥነት እየጨመረ ያለውን የወጣቶች ፍልሰት እንዲሁም በዚሁ መነሻ በከተሞች የሚፈጠረውን ማኅበራዊ ችግር አላስቀረም ብለዋል፡፡

አቶ እሸቱ አክለውም የዘርፉ ምሁራን ችግሩን ለመቅረፍ በሣይንሳዊ መንገድ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በመሥራት ለፖሊሲ አውጪዎች ምክረ ሀሳብ ሊሰጡ እንዲሁም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ላኪ አካባቢዎች በገጠር የልማት ሴክተሮች ላይ ትኩረት በመስጠት በላኪና በተቀባይ አገራት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ልዩነቶችን ማቀራረብ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

በጋሞ ዞን ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ የሥራ ስምሪት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ታረቀኝ ጌታቸው ባቀረቡት ሰነድ በዞኑ ያለው የፍልሰት ሁኔታ ከገጠር ወደ ከተማ በከፍተኛ የሥራ ፍለጋ፣ ከከተማ ወደ ገጠር በጡረታና ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እንዲሁም በመሬት ጥበት፣ በእርስ በርስ ግጭትና በአካባቢው መጥፎ ተግባር ፈፅሞ በባህሉ መሠረት አካባቢውን እንዲለቅ በህብረተሰቡ ሲወሰንበት ከገጠር ወደ ገጠር ፍልሰት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በዞኑ በፍልሰት ዙሪያ እየተሠሩ ያሉ ተግባራትን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡

ሌላኛው ተመራማሪ ዶ/ር ትዕግሥቱ አቡ ሲሆኑ በደቡብ ብ/ብ/ህ ክልል ህገ-ወጥ ፍልሰትን፣ በሰዎች መነገድንና ድንበር መሻገርን ለመከላከል በክልል ደረጃ የተሠሩ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሥራዎች ላይ ጥናት አቅርበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ አቶ ፍሬው ተስፋዬ በጋሞ ደጋማ አካባቢዎች ላይ ያለው ወቅታዊ የፍልሰት ሁኔታን ለማየት የሞከረ ቅድመ ዳሰሳ ጥናት አቅርበዋል፡፡ በዚህም በአካባቢዎቹ ላይ ከፍተኛ ፍልሰት መኖሩንና በአብዛኛው በአካባቢው ያሉ ሰዎች ወደ አዲስ አበባ እና በአርባ ምንጭ አቅራቢያ የሙዝ እርሻዎች ወዳሉበት አካባቢ እንደሚፈልሱና ፍልሰቶቹም ጊዜያዊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ ከትግራይና ከደቡብ ክልሎች ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ከህፃናትና ወጣቶች ቢሮ፣ ከዞን አስተዳደር፣ ከትምህርት መምሪያ፣ ከግብርና እና ከከተማ አስተዳደር፣ በጋሞ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች፣ ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር፣ ከወላይታ ሶዶና ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት እና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅቶች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት