የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሣይንስ ትምህርት ቤት በዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ/ም አዲስ ለተቀጠሩ 40 መምህራን ከኅዳር 1-5/2012 ዓ/ም ድረስ የማስተማር ክሂሎት ስልጠና ሰጥቷል፡፡

የትምህርት ቤቱ ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ እንደገለፁት የስልጠናው ዓላማ መምህራን ወደ ሥራው ዓለም በሚገቡበት ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ እንዲሁም አቅማቸው ጎልብቶ የመማር ማስተማሩን ሂደት በአግባቡ እንዲወጡ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መምህራኑ ከስልጠናው በተጨማሪ አጋዥ መጽሐፎችን በማንበብና የተሻሉ ልምዶችን በመውሰድ የማስተማር ክሂሎታቸውን አዳብረው የተማሪዎችንና የራሳቸውን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በሙሉ አቅም እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

በክፍል አያያዝ ላይ ስልጠና የሰጡት የስነ-ትምህርት ሣይንስ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ጴጥሮስ በቀለ መምህራን ወደ ክፍል ከመግባታቸው በፊት በሚያስተምሩት ትምህርት ዙሪያ በቂ ዝግጅት አድርገውና ከተማሪዎቻቸው ቀድመው በመገኘት አርዓያ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡

እንደ አሰልጣኙ ገለፃ የመምህራን በቂ ዕውቀት ያለመኖር፣ ተዘጋጅቶ አለመግባት፣ ሰዓት አለማክበር፣ አለባበስ፣ የፀጉር አቆራረጥ፣ ንፅህና እንዲሁም ተማሪዎችን በአንድ ዓይን አለማየት ለተማሪዎች አለመረጋጋትና ለክፍል ውስጥ ፀጥታ መደፍረስ ቁልፍ ምክንያቶች ሲሆኑ እነዚህም ጊዜያቸውን በአግባቡ ሳይጠቀሙና የሚፈልጉትን ነገር ሳያደርጉ ከክፍል እንዲወጡ ያስገድዳቸዋል ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በተማሪዎች በኩል ትምህርቱንና መምህሩን መጥላት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው በኩል የግብዓት እጥረት መኖር የስነ-ምግባር ችግር ያስከትላል ብለዋል፡፡

መ/ር ጴጥሮስ አክለውም መምህራን በአግባቡ አቅደውና በቂ ዝግጅት አድርገው ወደ ክፍል ከገቡ በራስ በመተማመን ማስተማርና ተማሪውም የሚፈልገውን ዕውቀት እንዲጨብጥ ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም መምህር በትምህርት ቤትም ሆነ ከትምህርት ቤት ውጪ ሁሌም የመልካም ነገር መሪ መሆን እንዳለበትና በማኅበረሰቡም ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው እንደሚገባ ጠቁመው ለተሳለጠ የትምህርት አሰጣጥ መ/ር ለተማሪው ተቆርቋሪ መሆን እንዳለበትና መቆርቆሩ ወደ አላስፈላጊ ነገር ሊመራው እንደማይገባ ገልፀዋል፡፡

ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል መ/ር መለሰ መንገሻ የእንግሊዝኛ ቋንቋን በመጠቀም በክፍል ውስጥ ማስተማር፣ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት፣ ትምህርቱ በሚሰጥት ወቅት፣ ከተሰጠ በኋላ እንዲሁም የክፍል አያያዝን መሠረት ያደረገ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ይህም በቀላል እንግሊዝኛ ሰዋሰውን አስተካክሎ መጠቀም፣ ምሳሌዎችንና አያያዦችን በአግባቡ በመጠቀም ተማሪዎችን ማስተማር እንዲችሉ የሚረዳ ነው፡፡ በተጨማሪም በመጀመሪያ ቀን ራስንና የትምህርት ይዘቱን ማስተዋወቅ እና የሚያረፍዱና ከክፍል የሚቀሩ ተማሪዎች አያያዝ በስልጠናው ትኩረት ተሰጥቶበታል፡፡ የማስተማር ስነ ዘዴ፣ የዕቅድ አዘገጃጀት፣ የምዘና መስፈርቶች እንዲሁም ከስነ ምግባር አኳያ ያለው አጠቃላይ ሁኔታም በዝርዝር ተዳሷል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው አንድ መምህር ወደ ክፍል ከመግባቱ በፊት የማስተማሪያ እቅድ ማቀድ፣ በቂ ዝግጅት ማድረግ፣ ለትምህርት ይዘቱ ማውጣት ያለበት ፈተና፣ የቋንቋ አጠቃቀም፣ ከተማሪዎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት፣ የሰዓት አጠቃቀምና አለባበስን ጨምሮ ትልቅ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት