31ኛውን ዓለም አቀፍ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን ምክንያት በማድረግ ‹‹ማኅበረሰቡ የለውጥ ኃይል ነዉ››፤ ‹‹ችግኞችን እንትከል፤ እንንከባከብ›› በሚል መሪ ቃል በአርባ ምጭ ከተማ ከኅብረት ለልማት ትማህርት ቤት እስከ አባያ ካምፓስ ድረስ ባለው አስፋልት መንገድ ግራና ቀኝ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ኅዳር 22/2012 ዓ.ም የችግኝ ተከላ አካሂዷል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ መኩሪያ 31ኛው ዓለም አቀፍ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን ‹‹ጥላቻንና ዘረኝነትን እናስወግድ ራሳችንና ማኅበረሰባችንን ከኤች አይ ቪ/ኤድስ እንጠብቅ፤ ከተማችንን አረንጓዴ እናድርግ!!›› በሚል መሪ ቃል በሁሉም ካምፓስ ካሉ ተማሪዎች ጋር ሲከበር መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በማጠቃለያ ፕሮግራሙም ከተማሪዎች፣ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ከከተማው ህዝብ ጋር ‹‹ኑ አብረን ችግኝ እንትከል ፤ እንከባከባቸው›› በሚል መሪ ቃል መከበሩን ተናግረዋል፡፡ ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከል እያንዳንዱ ግለሰብ ራሱን ቢጠብቅ ቤተሰቡን፣ ማኅበረሰቡንና አገሩን በመጠበቅ በዓለም ደረጃ ዜሮ ማድረስ ይቻላልም ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠዉ ዳርዛ መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ 31ኛውን የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን ምክንያት በማድረግ የችግኝ ተከላ ስናካሂድ በከተማችን ብሎም በአገራችን ከኤች አይ ቪ/ኤድስ ነፃ የሆነ ትውልድ እንዲኖር እንዲሁም ከተማችን ጽዱ፣ አረንጓዴና ለዜጎች ምቹ መኖሪያ እንድትሆን በማሰብ ነው ብለዋል፡፡ ስለሆነም ማኅበረሰቡ ሐምሌ 22/ 2011 ዓ/ም የተተከሉትን ችግኞች ጨምሮ ከእንስሳት ንክኪና ከሌሎች ጉዳቶች እንዲከላከል፣ እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ ጠይቀዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው አብዛኛው ማኅበረሰብ በበሽታው መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች ዙሪያ በቂ እውቀት ቢኖረውም በመዘናጋት ምክንያት በሽታው እየተስፋፋ መሆኑን ጠቅሰው ሥርጭቱን ለመግታት ኅብረተሰቡ ራሱን በመጠበቅ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የአገልግሎት ጽ/ቤት ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ቶንጃ ፕሮግራሙ በዋናነት ኅብረተሰቡ ራሱን ከኤች አይ ቪ/ኤድስ እንዲጠብቅ መነቃቃትን ከመፍጠሩ ጎን ለጎን ከተማዋ ጽዱና አረንጓዴ እንድትሆን ችግኝ በመትከል አሻራውን እንዲያሳርፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት