ዩኒቨርሲቲው ከሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከጥቅምት 1-15/2012 ዓ/ም ለነባርና አዲስ ገቢ ተማሪዎች የሥነ-ምግባር መመሪያ አተገባበርን በተመለከተ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት ባለፈው ዓመት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አላስፈላጊ ግጭቶች ተከስተው የመማር-ማስተማር ሂደት እንዲስተጓጎል በማድረጉ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 1152/2011 አንቀጽ 86 ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሥነ-ምግባር መመሪያ አዘጋጅቶ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለነባርና አዲስ ገቢ ተማሪዎች ስልጠና እንዲሰጥ ወስኗል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በሙሉ ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቦ ምላሸ የሚሹ ጥያቄዎች ሲኖሩ በአግባቡ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ መፍትሄ እንዲሰጥ ማድረግ እንዳለባቸው ዶ/ር አለማየሁ አሳስበዋል፡፡ ተማሪዎችም ከስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር በትምህርታቸው ስኬታማና የመልካም ሥነ-ምግባር ባለቤት ሆነው ለራሳቸው፣ ለአገራቸውና ለቤተሰቦቻቸው የሚጠቅሙ መልካም ዜጎች እንዲሆኑም መልዕክታቸው አስተላልፈዋል፡፡

የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል በበኩላቸው የሥነ-ምግባር መመሪያው ተማሪዎችን በጥሩ ሁኔታ የሚያንጽ በመሆኑ በመመሪያው ዙሪያ ተማሪዎች በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸውና አከራካሪ ወይም ማብራሪያ የሚፈልጉ ነጥቦች ሲያጋጥሙ መመሪያና ደንብ አክብረው ሊጠይቁ ይገባል ብለዋል፡፡

አንድ ተማሪ የሥነ-ምግባር ጥሰት ፈጸመ የሚባለው በተቋሙ፣ በሠራተኞችና በሌሎች ተማሪዎች መደበኛ እንቅስቃሴና ሥራ ላይ ተገቢ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት የሚፈጥር፣ የሌሎች የተቋሙ ማኅበረሰብ አባላትን መብት የሚጋፋ፣ መልካም ግንኙነትን የሚጥስ ወይም ተቋሙን የሚጎዳ ድርጊት ሲፈጽም እንደሆነ በመመሪያው ላይ በዝርዘር እንደተቀመጠ ዶ/ር አብደላ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በግቢ ውስጥ በቡድን ሆኖ ማንኛውንም ዓይነት ኃይማኖታዊም ሆነ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ኃይማኖትን፣ ብሔርን፣ ባህልንና ቋንቋን የሚያንቋሽሸ ንግግር መናገር፣ መጻፍ ወይም ድርጊት መፈጸም እንዲሁም በአገልግሎት ዙሪያ ቅሬታ ሲኖር ሠላማዊ እና ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ ከመጠየቅ ይልቅ አመጽ ማንሳት፣ ማስነሳትና መተባበር አይፈቀድም፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ችግሮች እንዳሉ በተማሪዎች በኩል ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሸና ሰፊ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን መምህራን ለተማሪዎች አርኣያ መሆን እንዳለባቸው ስለሚታመን በተማሪዎች የሥነ-ምግባር መመሪያ ዙሪያ ከመምህራን ጋር ውይይት እንደሚኖር ዶ/ር አብደላ ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎች ስልጠናው በጣም ጠቃሚ እንደሆነና በአገልግሎት ዘርፍ ለተነሱ ጥያቄዎች ዩኒቨርሲቲው ወቅቱን ጠብቆ ምላሸ እንዲሰጥ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት