በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሲቪል ምኅንድስና ፋካልቲ በሥሩ ለሚገኙ መምህራንና ተማሪዎች ለኮንስትራክሸን ኢንዱስትሪ ጠቃሚ በሆኑ አዳዲስ ሶፍትዌሮች ዙሪያ ከጥቅምት 22 - ኅዳር 20/2012 ዓ/ም ለ5 ተከታታይ ቅዳሜ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ በሥልጠናው ላይ መምህራንን ጨምሮ ከ150 በላይ የቅድመ ምረቃና የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በወቅቱ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትና ሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ስልጠናው በተግባር የተደገፈ በመሆኑ የትምህርት ጥራትን ለማሳለጥና የሥርዓተ-ትምህርቱን ግብ ለማሳካት የጎላ ድርሻ እንዳለው ገልፀው ሥልጠናው በተሳካ ሁኔታ እንዲሰጥ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው በተግባር የተደገፈ ሥልጠና መስጠቱ የመምህራንንና የተማሪዎችን አቅም በማጎልበትና ከቴክኖሎጂው ጋር በማዘመን በዘርፉ ያለውን ተግዳሮት ለመፍታት ያስችላል ብለዋል፡፡ ስልጠናው ለሌሎች የትምህርት ክፍሎች እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናው ለጥናትና ምርምር በ‹SPSS›፤ ለስትራክቸራል ምኅንድስና በ‹SAP›፣ ‹ETABS› እና ‹STAAD PRO›፤ ለጂኦቴክኒካል ምኅንድስና በ‹Geo Studio›፤ ለመንገድና ትራንስፖርት ምኅንድስና በ‹MX road›፣ ‹Eagle point›፣ ‹HDM-4› እና ‹PTV-VISUM› እንዲሁም ለቅየሳ ምኅንድስና በ‹ERDAS›፣ ‹ARC› እና ‹GIS› ሶፍትዌሮች ላይ ያተኮረ መሆኑን የሲቪል ምኅንድስና ፋካልቲ ዲን አቶ ሀብታሙ መለሰ ገልጸዋል፡፡

የአዳዲስ ሶፍትዌሮች ሥልጠና የመምህራንና ተማሪዎችን አቅም ለማጎልበት በተለይም የመመረቂያ ጽሑፋቸውን ለሚያዘጋጁ የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች ወሳኝ እንደሆነ አሰልጣኞች ተናግረዋል፡፡ ሠልጣኞቹ ያገኙትን ዕውቀትና ክሂሎት በልምምድ ማዳበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ሠልጣኞቹ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በጽንሰ-ሐሳብ ደረጃ ክፍል ውስጥ የተማሩትን በተግባር ልምምድ ማድረጋቸው በዘርፉ የላቀ ዕውቀትና ክሂሎት ለማዳበር ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት