ዩኒቨርሲቲው ለ6ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 140 የሕክምና ዶክተሮች ታኅሣሥ 11/2012 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 37ቱ ሴቶች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በአገሪቱ ለኅብረተሰቡ ጤና መሻሻል መንግሥት እያደረገ ለሚገኘው ርብርብ ስኬታማነት የተመራቂዎቹ አስተዋፅኦ ጉልህ በመሆኑ በተመረቁበት ዘርፍ በሙሉ አቅማቸው በማገልገል ለአገራችን ህዳሴ ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

በቀጣይ ከነባራዊው የሥራ ዓለም የሚያካብቱትን ልምድ ከዩኒቨርሲቲው ከገበዩት ዕውቀትና ክሂሎት ጋር በማዋሃድ በተመረቁበት ዘርፍ የበቃ ባለሙያ የመሆን ዕድል የሚጠብቃቸው መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ በተሻለ የሥራ አፈፃፀም፣ በማንበብና በመመራመር ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ለማደግ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ይናገር ደሴ ባስተላለፉት የሥራ መመሪያ ተመራቂዎች የትምህርት ቆይታቸው ረዘም ያለ ቢሆንም የነገውን ተስፋ አሻግረው በማየት የገጠሟቸውን ውጣ ውረዶች በትጋትና በፅናት በመቋቋም ለዛሬው ስኬት መብቃታቸው የሚያኮራ መሆኑን ጠቅሰው ዋናው የውጤት መለኪያ ሕብረተሰቡን ማገልገል በመሆኑ በዚህ ረገድ ተማሪዎቹ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ የሚደረጉት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የአገራችንን የለውጥ ተስፋ ያሳዩ ቢሆንም በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ማጋጠማቸው ስለማይቀር እነዚህን በጋራ ተቋቁመን የአገራችን ደኅንነት፣ ሰላም እና ልማት እንዲረጋገጥ የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡ ተመራቂዎቹ የሥራ ዘመናቸውና ህይወታቸው የተሳካ እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ በድሩ ሂሪጎ የሕክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመማር ማስተማር ባሻገር በአገር አቀፍ ምርምርና መድኃኒት አስተዳደር ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሌሎች የጤና ተቋማት ጋር በቅንጅት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

3.78 በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነው ተመራቂ ዶ/ር ፍቅሩ ደመቀ ቆይታው ውጣ ውረድ የበዛበት እንዲሁም ጊዜንና አቅምን አሟጦ መጠቀምን የሚፈልግ ቢሆንም ህልሙ በመሳካቱ መደሰቱን ገልጿል፡፡ ማኅበረሰቡ ከእኛ ብዙ የሚጠብቅ በመሆኑ ዛሬ ያከማቸነውን እውቀት ተጠቅመን የሚጠብቀንን ማኅበረሰብ በጥንቃቄና በማስተዋል መርዳት ይኖርብናል ብሏል፡፡

3.72 በማምጣት ከአጠቃላይ ተመራቂዎች 2ኛ እና ከሴቶች 1ኛ በመሆን ልዩ ተሸላሚ የሆነችው የማዕረግ ተመራቂ ዶ/ር ኢክራም ሙሳ በተማርኩበት ሙያ የገጠሩን ማኅበረሰብ ለማገልገል ዕቅዱ አለኝ ብላለች፡፡ በተጨማሪም የሕክምና ሙያ ፆታን የሚለይ ባለመሆኑ ሁሉም ሰው በርትቶ ከሠራ የተሻለ ውጤት በማምጣት ካሰበው እንደሚደርስ ተናግራለች፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት