‹‹ሁለንተናዊ ልማታችንንና ሠላማችንን ለማረጋገጥ በሙስና ላይ እንዝመት፤ ጊዜው የተግባር ነው!›› በሚል መሪ ቃል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ቀን ታኅሣሥ 21/2012 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡ በዓሉ ሲከበር በዓለም ለ16ኛ በኢትዮጵያ ለ15ኛ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ለ6ኛ ጊዜ ነው፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው ሙስና ለሠላማዊ ኑሮ በመሆን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት በተሞላበት መንፈስ በቁርጠኝነት አጥብቆ መታገል ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሙስናን ለመዋጋትና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነ ፕሬዝደንቱ ገልፀው ውይይቱ በሠራተኞች ዘንድ መልካም ሥነ-ምግባርን ከመገንባት ባለፈ በሙስና ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡ የሥነ-ምግባር መጓደል የሚንፀባረቅባቸው ሠራተኞችና በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚሞክሩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ዮሰፍ ወርቁ በበኩላቸው ሙስናና ብልሹ አሠራርን በመታገል ሠራተኞች 12ቱን የሥነ-ምግባር መርሆዎች ማክበር አለባቸው ብለዋል፡፡ በሥነ-ምግባር የጎለበቱ ሠራተኞችን በማፍራት ረገድ ሰፊ ሥራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ ከህግ እና ከሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ክፍሎች የተወጣጡ መምህራን ለውይይት የሚሆን መነሻ ሀሳብ አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በውይይቱ ላይ ሙስናና ብልሹ አሠራርን በመጸየፍ ህዝባዊ ወገንተኝነትን ማሳየት ተገቢ እንደሆነና የሴቶችን እኩልነት ማክበር፣ ፆታዊ ጥቃትን መከላከል፣ በሥነ-ምግባር የጎለበቱ ሠራተኞችን ማፍራት እንዲሁም ሠራተኞችን በእውቀትና በክሂሎት ለተቋማዊ ለውጥና ዕድገት ማብቃት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሠራተኞችን በመልካም ሥነ-ምግባር በማነፅ ጠንካራና ለሌሎች ሠራተኞች አርኣያ የሆኑትን በመሸለም ሙስናን መታገል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የተበላሸ የፖለቲካ ሥርዓት ለሙስና መበራከት ምክንያት እንደሆነ ገልጸው አገራዊ ለውጥን ተከትለው የሚመጡ አንዳንድ ጠቃሚ የሀሳብና የአሠራር ለውጦችን በመተግበር የህዝቡን ፍላጎት የሚያረካ ምላሽ በመስጠት ቀልጣፋና ፈጣን የአሠራር ሥርዓትን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በበዓሉ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ሠራተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት