እ.አ.አ ከ2015 ዓ/ም ጀምሮ ለ4 ዓመታት ሲካሄድ የቆየው የVLIR እንሰት ፕሮጀክት የማጠቃለያ ወርክሾፕ ጥር 12/2012 ዓ/ም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡ በፕሮጀክቱ አማካይነት በጋሞ ደጋማ አካባቢዎች በእንሰት አመራረት ሂደትና በእንሰት አጠውላጊ በሽታ ዙሪያ የተደረጉ የምርምር ሥራዎች ቀርበዋል፡፡ በዕለቱ ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ባዮ-ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባባር የእንሰት ምርት አዘገጃጀትና ድኅረ-ምርት አያያዝን በቴክኖሎጂ ፈጠራዎች የሚያግዝ አዲስ ፕሮጀክትም ይፋ አድርጓል፡፡ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

ፕሮግራሙን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንሰት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ፣ ከመድኃኒትነት እንዲሁም የመሬት መሸርሸርን ከመቀነስ አንፃር ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሰብል እንደሆነ ጠቁመው ተክሉ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታዎችን በመቋቋም ጭምር ምርት መስጠት የሚችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የእንሰት አመራረት ሂደትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ሊሠጠው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በእንሰት አጠውላጊ በሽታ ዙሪያ የምርምር ሥራቸውን ያከናወኑት አቶ ሳቡራ ሻራ በሽታው ኢትዮጵያ ውስጥ በእንሰት ተክል ላይ ከሚታዩ ችግሮች መካከል ቁጥር አንድ መሆኑን ገልፀው በሽታው የእንሰት ቅጠልን ከማጠውለግ ጀምሮ ተክሉን በማድረቅ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ እንደ አቶ ሳቡራ ገለፃ በምርምራቸው በሽታውን መቋቋም የሚችል ዝርያ መኖሩንና አለመኖሩን እንዲሁም በሽታው በተለያየ የአየር ንብረትና ከባቢ ውስጥ ያለውን የሥርጭት ሁኔታ መለየት ላይ ትኩረት አድርገው ሥራቸውን እንዳከናወኑ ተናግረዋል፡፡

በሽታው ሁሉም የእንሰት ዝርያዎች ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ማረጋገጥ እንደቻሉ የተናገሩት ተመራማሪው ከዚህም ባሻገር የመሬት ከፍታቸው ዝቅተኛ በሆኑ አካባቢዎች የበሽታው ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚታይ ነገር ግን ከባሕር ጠለል በላይ ከፍ እያልን በሄድን ቁጥር የበሽታው ሥርጭት እየቀነሰ እንደሚሄድ ማረጋገጥ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ከመጠን በላይ ማዳበሪያ መጠቀምም በተወሰነ ደረጃ ለበሽታው መስፋፋት አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡ ስለበሽታው ምልክቶች፣ መተላለፊያ መንገዶችና ጥንቃቄዎች ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም በእንሰት ማሳ ውስጥ የማዳበሪያ አጠቃቀምን የመመጠን ጉዳይ በቀጣይ በትኩረት ሊሠሩ የሚገባቸው ጉዳዮች መሆን እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡

ሌላኛው በእንሰት ምርት አዘገጃጀትና የድኅረ-ምርት አያያዝና አጠቃቀም ላይ አትኩረው የምርምር ሥራቸውን ያከናወኑት ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ከ20 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን እንሰትን ለምግብነት እንደሚጠቀሙ ገልፀው መንግሥት በፖሊሲ ደረጃም ሆነ በተግባር የሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ በመላ አገሪቱ የእንሰት ምርት አዘገጃጀትና የድኅረ-ምርት አያያዝና አጠቃቀም ባህላዊና ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ባለመሆኑ በምርት ጥራትና ብዛት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ አሉታዊ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

በእንሰት ምርት አዘገጃጀት ሂደት እንሰቱን ወደ ምግብነት ለመቀየር የሚደረገው የማብላላት( Fermentaion) ሂደት ዋነኛው መሆኑን ጠቁመው ሂደቱ ከ2-3 ወር ይፈጃል ብለዋል፡፡ በምርምራቸው ይህንን ረጅም የማብለያ ጊዜ የሚቀንስ ጥራቱን፣

ጣዕሙና ሽታውን የጠበቀ ምርት በሙከራ ማግኘት የሚያስችልና የማብላላት ሂደቱን ከ7-10 ቀን ብቻ የሚያሳጥር አዲስ እርሾ/starter culture/ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህንን እርሾ ማምረት በሴቶች ላይ ከፍተኛ የሥራ ጫና የሚቀንስ ስለሆነ ለአርሶ አደሩ ቴክኖሎጂውን የማዳረስ ሥራ አዲስ የተጀመረው ፕሮጀክት አካል ሆኖ እንደሚሠራም ተመራማሪው ተናግረዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ባዮ-ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንዱስትሪያል ባዮ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የዘርፉ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶ/ር ፋንታሁን ወ/ሰንበት በበኩላቸው በፕሮጀክቱ ተሠርተው የቀረቡት የምርምር ሥራዎች የእንሰት ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ጥራት በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው በተለይ በድኅረ-ምርት አያያዝና አጠቃቀም ሂደት ውስጥ ያለውን ኋላ ቀርና ባህላዊ አሠራር ከማስቀረት አኳያም ጠቀሜታቸው ሰፊ ነው ብለዋል፡፡ አዲስ ለተጀመረው ፕሮጀክት ተፈጻሚነት መሥሪያ ቤታቸው በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

አዲሱ ፕሮጀክት ለ3 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ለሥራው ማስፈፀሚያ የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 4 ሚሊየን ብር መመደቡ ታውቋል፡፡ በፕሮጀክቱ የእንሰት ምርት አዘገጃጀትና ድኅረ-ምርት ሂደትን ለማዘመን የሚረዱ የመፍጫ፣ መጭመቂያ፣ መቁረጫና ሌሎች የተለያዩ የማቆያ ቴክኖሎጂዎች በጋሞ እንሰት አምራች አካባቢዎች ተሞክረው ውጤታማነታቸው ተረጋግጦ በመላ አገሪቱ እንዲሰራጩ ይደረጋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት