የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የማስተማሪያና ሪፌራል ሆስፒታሉን ጨምሮ ቀደም ሲል ከነበረው አደረጃጀት ከፍ ባለ ደረጃ እንዲደራጅ ተጠንቶ ተወስኗል፡፡ በዚህ መሠረት ኮሌጁ በ‹ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር› እንዲመራ የዩኒቨርቲው የሥራ አመራር ቦርድ ታኅሣሥ 10/2012 ዓ/ም ባካሄደው ስብሰባ ወስኗል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

በመዋቅር ለውጡ የሕክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ዲን የነበሩት ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የኮሌጁ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡ ኮሌጁ የሕክምና ት/ቤት፣ ሌሎች የጤና ሣይንስ ዘርፎችንና የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታልን ጨምሮ 4 ዋና ዘርፎችን የሚመሩ ኤክስክዩቲቭ አካዳሚክ ጉዳይ ዳይሬክተር፣ የምርምርና ማኅበረሰብ አገ/ት ዳይሬክተር፣ ክሊኒካል ዳይሬክተር እና የአስተዳደር ጉዳይ ዳይሬክተር በሥሩ ይኖሩታል፡፡

በኮሌጁ በቀጣይ የድህረ-ምረቃ ትምህርት ቤት ለመገንባት የታቀደ ሲሆን በተለይም የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታሉን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተመራጭ የሕክምና ተቋም ለማድረግ አስፈላጊውን ግብዓት የማሟላት ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ዶ/ር ታምሩ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ታምሩ የመዋቅር ለውጡን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት መዋቅሩ ከዚህ በፊት የነበረውን የሥራ ጫና ለማቃለልና ሥራዎችን በተቀላጠፈ መልኩ ለመሥራት ያግዛል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የትምህርት ጥራትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በየደረጃው በመወያየት ለመፍታት አዲሱ መዋቅር የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በ2000 ዓ/ም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና ዶክትሬት ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን በወቅቱ ባስመዘገቡት የላቀ ውጤት ዩኒቨርሲቲው በሰጣቸው ዕድል የኢንተርናል ሜዲስን ስፔሺያላይዜሽን ትምህርታቸውን 2003 ዓ/ም አጠናቀዋል፡፡ በ2004 ዓ/ም አርባ ምንጭ ሆስፒታል ሥራ የጀመሩት ዶ/ር ታምሩ ከሕክምና ሥራቸው ጎን ለጎን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ ከኅዳር 1/2006 ዓ/ም- ታኅሣሥ 20/2007 ዓ/ም የሕክምና ት/ቤት ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን ከኅዳር/2009 ዓ.ም - ታኅሣሥ/2012 ዓ.ም የኮሌጁ ዲን እንዲሁም ከታኅሣሥ/2012 ዓ.ም ጀምሮ በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የኮሌጁ ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ይገኛል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት