የዩኒቨርሲቲው የ2012 ትምህርት ዘመን የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም የካውንስል አባላት በተገኙበት ጥር 16/2012 ዓ/ም ተገምግሟል፡፡

ባለፉት 6 ወራት ውስጥ በሁሉም ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን ለመፈተሽ፣ ደካማና ጠንካራ ጎኖችን ለመለየት እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የውይይት መድረኩ የተዘጋጀ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልፀዋል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የስትራቴጂክ ዕ/ዝ/ት/ክ ዳይሬክተሬት ዳይሬክተር አቶ አስፋው ደምሴ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተመለከተው ሠላማዊ መማር ማስተማርን ለማስፈን ከሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በተላከው የአፈጻጸም መመሪያ መሠረት የተማሪዎች ኅብረትና ሥራ አስፈፃሚዎች ምርጫ መከናወኑ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስንና የሥነ -ተዋልዶ ጤና ችግሮችን ወደ ዜሮ ለማምጣት በዋናው ግቢ የተገነባው የዜሮ ፕላንና የኢንፎኪን ማዕከል መመረቁና የፀረ- ኤድስ ክበብ እንዲጠናከር መደረጉ፣ አዲስ ለተቀጠሩ የዩኒቨርሲቲው መምህራን በማስተማር ክሂሎት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህራን የሙያ ሥነ-ምግባርና የእንግሊዝኛ ቋንቋ የክፍል ውስጥ አጠቃቀም ላይ ስልጠና መሰጠቱ፣ የቤተ-መጽሐፍት ስምንት አዳራሾችና የማንበቢያ ሥፍራዎች ንፁህና ለአገልግሎት ምቹ መደረጋቸው፣ የቤተ-መጽሐፍት አገልግሎትን ለማሻሻል 15,600 ሶፍት ኮፒ፣ 85,000 መጽሐፍት፣ 1,600 የመመረቂያ እና የምርምር ጽሑፎች ከመምህራን በማሰባሰብ ለንባብ ዝግጁ መደረጋቸው እንዲሁም የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ መካሄዱ በ6 ወራት ውስጥ ከታዩ መልካም አፈፃፀሞች መካከል ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም በግርጫ የደጋ ፍራፍሬና አትክልት ምርምር ማዕከል በምርምር የተገኘ ምርጥ የድንች ዝርያ ከአካባቢው የአየር ፀባይና አፈር ሁኔታ ጋር በማለማመድ ለሁለት ቀበሌያት አርሶ አደሮች መከፋፈሉ፣ በ 7 ነባርና 4 አዲስ የተከፈቱ የጎልማሶች ትምህርት ማዕከላት 709 ጎልማሶች በደረጃ 1 እና በደረጃ 2 በመማር ላይ መሆናቸው፣ ለሰባት ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤቶችና ለሦስት ወጣቶች ማዕከላት ለእያንዳንዳቸዉ 340 መጽሐፍት ድጋፍ መደረጉ፣ ሐምሌ 22 በአረንጓዴ አሻራ ቀንና ከዚያ በኋላ ከተተከሉ ችግኞች 94 ከመቶ የሚሆኑት መፅደቃቸው፣ በSTEM ፕሮጀክት ከአምስት ዞኖችና ከአንድ ልዩ ወረዳ ለተወጣጡ 320 ተማሪዎች በሣይንስ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግ እና በሂሳብ ትምህርቶች የተግባር ሥልጠና በአግባቡ መሰጠቱ፣ ለ1,400 የሴክተር መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ለ25 ሰዓታት የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም (Digital Literacy) ስልጠና መሰጠቱ እና ሁለት የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች የፕሮቶታይፕ ሥራቸዉ አልቆ ወደ ተጠቃሚው እንዲደርሱ መደረጉ ሌሎች በግማሽ ዓመቱ ውስጥ የታዩ መልካም አፈፃፀሞች ናቸው፡፡

የተማሪዎች ጤናን በሚመለከት የ24 ሰዓት አገልግሎት እንዲያገኙና በሁሉም ክሊኒኮች የሕክምና ዶክተሮች ሙያዊ እገዛ እንዲሰጡ መደረጉ፣ የመምህራንና የቴክኒክ ድጋፍ ሰጪ እንዲሁም የአስተዳደር ሠራተኞች አዲሱ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉ፣ ከውስጥ ገቢ ከዕቅድ በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉ፣ በዋናው ግቢ የመሰብሰቢያ አዳራሽና ክሊኒክ፣ በጫሞና አባያ ካምፓሶች ቤተ-መጽሐፍትና ቤተ-ሙከራ እንዲሁም የመምህራን ቢሮ ግንባታዎች ተጠናቀው ጊዜያዊ ርክክብ መደረጉ ሌሎች በ6ቱ ወራት ውስጥ የታዩ መልካም ተግባራት ናቸው፡፡

በዩኒቨርሲቲው ከካምፓሶች ብዛትና የሥራ ስፋት አንጻር እንዲሁም በርካታ ተሽከርካሪዎች ያረጁ በመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ የተሸከርካሪ እጥረት መከሰት እንዲሁም የግዥ አፈፃፀም ዘመናዊና ቀልጣፋ አለመሆን ጋር ተያይዞ ለመማር ማስተማር፣ ምርምርና ለቢሮ ሥራዎች መቅረብ የሚገባቸው ግብዓቶች በወቅቱ ባለመቅረባቸው በሥራዎች አፈፃፀም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደራቸው፣ ከአዲሱ የሠራተኞች ምደባ ጋር ተያይዞ እንደ ተማሪዎች ምግብ ቤት ባሉ የሥራ መደቦች የሠራተኛ ማነስ መታየቱ እንዲሁም የመንግሥትና የተማሪዎችን ንብረት የሚሰርቁ ሌቦች ተይዘው ለሚመለከተው አካል ሲቀርቡ በቂና አስተማሪ እርምጃ አለመወሰዱ በግማሽ ዓመቱ ውስጥ እንደ ዋነኛ ችግሮች ተጠቅሰዋል፡፡

ሰላማዊ መማር ማስተማር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከተማሪ አደረጃጀቶች፣ ከአካባቢው መስተዳድርና ከኅብረተሰቡ ጋር ያለውን ትስስር አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የትምህርት ጥራትና መልካም አስተዳደር ፎረም ውይይቶችን በማጠናከር ከተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ጋር ከሚካሄዱ ውይይቶች ግብዓት በመውሰድ ክፍተቶችን ማስተካከል፣ የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስርን አጠናክሮ መቀጠል፣ ከኦዲት ግኝት የፀዳ ተቋም ለመሆን በትኩረት መሥራት፣ የገቢ ማመንጫ አማራጮችን በማበራከትና አሠራሮችን በማሻሻል ገቢን ማሳደግ፣ የምርምር ሥራ ውጤቶችና የተላመዱና የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተጠቃሚው ማኅበረሰብ የማሸጋገር ሥራን አጠናክሮ መሥራት፣ የግዥ ሥራ አፈጻጸምንና ሌሎች መሰል ጉዳቶችን የመጓተት ሁኔታን ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ማሻሻል የሚሉት በቀጣይ በትኩረት ሊሠሩ የሚገቡ ተግባራት መሆናቸው በውይይቱ ወቅት ተመልክቷል፡፡