በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት አስተባባሪነት በደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከል 2ኛው የባህል ፊልም ፌስቲቫል ከየካቲት 14-15 2012 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ በፌስቲቫሉ ‹‹በጋሞ ከፍተኛ አካባቢ የእንሰት አመራረት››፣ ‹‹የጤፍ ዳንስ›› (በትግራይ ከፍተኛ ቦታ የጤፍ አመራረት)፣ ‹‹አብርሃምና ሣራ›› (በሰሜን ኢትዮጵያ ጉንዳጉንዶ አካባቢ ማኅበረስብ ላይ ያተኮረ) እና ‹‹የሐመር ቤተሰብ›› በሚሉ ርዕሶች የተሠሩ ፊልሞች ቀርበዋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በብዝሃ ሀብት፣ በባህልና በአኗኗር ዘይቤ ትልቅ አገር ብትሆንም የዓለም ህዝብ እንዲሁም አንዱ ማኅበረሰብ ሌላኛውን በሚገባ አያውቀውም፡፡ ከዚህም ባሻገር ባህልና የአኗኗር ዘይቤው በተለያዩ ምክንያቶች እየተበረዘና እየጠፋ ስለሆነ በሣይንሳዊ መንገድ ፊልም በማዘጋጀት ማስተዋወቅና በመረጃ መልክ በማስቀረት መጪው ትውልድ ባህሉን፣ የአኗኗር ዘይቤውንና የቀደመው ማኅበረሰብ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ጥብቅ ትስስር እንዲያውቅ ፊልሞቹ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹በጋሞ ከፍተኛ አካባቢ የእንሰት አመራረት›› ፊልምን ካዘጋጁት አንዱ የሆኑት በዩኒቨርሲቲው ሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ኢዮብ ደፈርሻ እንደገለጹት እንሰት በጋሞ ከፍተኛ አካባቢ የሚበቅል ተክል ሲሆን ለሰው ምግብነት፣ ለእንስሳት መኖነትና ለተፈጥሮ ማዳበሪያነት የሚያገለግልና በአብዛኛው በክረምት ሌሎች ጥራጥሬ እህሎች እስኪደርሱ የሚያቆይ ነው፡፡

እንደ መምህር ኢዮብ ገለጻ በአካባቢው ድርቅ ሲከሰት ማኅበረሰቡ በረሃብ እንዳይጠቃና እንስሳት በድርቁ እንዳይጎዱ ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ተክሉ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ሰብሎች እየተተካ በመሆኑ ጨርሶ እንዳይጠፋ ለመጠበቅ፣ በሌሎች ማኅበረሰቦች ዘንድ እንዲታወቅና ለመጪው ትውልድ በመረጃ መልክ ለማስቀመጥ ታስቦ ፊልሙ ተሠርቷል፡፡

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የፌስቲቫሉ ተሳታፊ አቶ ወሊ ኃይሌ ከፌስቲቫሉ የምርምር መነሻ ሀሳቦችን፣ በሌሎች ማኅበረሰቦች ውስጥ ያሉ እሴቶችን፣ ባህልን በምርምር የመግለጽና ለትውልድ የማስተላለፍ ዘዴን እንዲሁም የምርምር ጽሑፍ በፊልም መልክ ሲቀርብ ታዳሚው በቀላሉ ሊረዳው እንደሚችል መገንዘብ ችያለሁ ብለዋል፡፡

የደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የቆየ ሲሆን ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥር እየተዳደረ እንደሚገኝ የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ መንግሥቱ ገልጸዋል፡፡ ማዕከሉ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ባሉ ባህሎችና በተለያዩ ሰብሎች ላይ ጥናት በማድረግ ማሳወቅ፣ መጠበቅና መንከባከብ ላይ ይሠራል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት