የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቤኔፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮግራም የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማስጠበቅና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በአርባ ምንጭ ክላስተር በምዕራብ አባያ፣ ደራሼ፣ ዛላና ቁጫ ወረዳዎች በሚገኙ 16 ቀበሌያት ምርጥ ዘሮችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የፕሮግራሙ አስተባባሪ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ እንደገለጹት የፕሮጀክቱ ዓላማ መልካም ተሞክሮዎችንና የተለያዩ ዝርያዎችን ከምርምር ጣቢያዎች በማምጣት የሴፍቲኔት ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

እንደ ዶ/ር መብራቱ ማብራሪያ ‹‹BH-547›› የበቆሎ ምርጥ ዝርያ በ4ቱም ወረዳዎች በ160 አርሶ አደሮች እንዲሁም ‹‹በለጠ›› እና ‹‹ጉደኔ› የተሰኙ የድቡልቡል ድንች ዝርያዎች በ90 አርሶ አደሮች ሙከራ ተደርጎባቸው አስደሳች ውጤት የተመዘገበ ሲሆን 6 ዓይነት የማሽላ ዝርያዎች ተሞክረው ‹‹መኮ›› እና ‹‹መልካም›› የሚባሉት የተሻለ ውጤት አስገኝተዋል፡፡ በተጨማሪም ከጓሮ አትክልቶች ጥቅል ጎመን፣ ካሮት፣ ቀይ ስር፣ ቆስጣ፣ የቫይታሚን A ይዘቱ ከፍተኛ የሆነ ብርቱካናማ ቀለም ያለው ስኳር ድንች እንዲሁም ከፍራፍሬ የፓፓያ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ሠርቶ ማሳያዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ እስከ አሁን ባለው ሂደት 1,532 አርሶ አደሮች በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል 49.6 በመቶው ሴቶች ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት በሰርቶ ማሳያው አርሶ አደሩ የተሻለውን ዝርያ እንዲመርጥ የተደረገ ሲሆን በዚሁ ዓመት የቅደመ ማስፋፊያ ሥራዎች የሚሠሩና ለበርካታ አርሶ አደሮች ተደራሽ የሚደረጉ ይሆናል፡፡ ዝርያዎቹን ለአርሶ አደሮች በሰፊው ለማድረስ ከዞንና ከወረዳ ግብርና ጽ/ቤቶች፣ ከክልል ግብርና ቢሮና አደጋ መከላከል ኮሚሽን እንዲሁም ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር እየሠሩ መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

በደራሼና ዛላ ወረዳዎች የሚገኙ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት የቀረቡላቸው የበቆሎ፣ የማሽላ፣ የቦለቄ እና የጓሮ አትክልት ምርጥ ዝርያዎች በአጭር ጊዜ የሚደርሱና በቀላሉ ከጓሯቸው የሚገኙ በመሆናቸው ቤተሰቦቻቸውን በቀላሉ ለመመገብ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል፡፡ በተለይ ብርቱካናማ ቀለም ያለው የስኳር ድንች ዝርያ በጣም ጠቃሚ የምግብ ይዘት ያለውና ፈጥኖ ደራሽ በመሆኑ ከማሳቸው አልፎ ግቢያቸው ውስጥ መትከላቸውን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በሠርቶ ማሳያ ቦታዎች ዝርያዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማምረትና ተጠቃሚ መሆን የሚያስችሉ ስልጠናዎችን ከመስጠት ጀምሮ እያደረገ ላለው አስተዋፅኦ አመስግነው ዝርያዎቹ በስፋት ይቀርቡ ዘንድም ጠይቀዋል፡፡

በደራሼ ወረዳ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽ/ቤት የምግብ ዋስትና ቡድን መሪ አቶ አብርሃም ኩታሎ አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ ፕሮጀክቱ እያመጣልን ያለው በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ ምርጥ ዝርያዎች በጣም ተጠቃሚ አድርገውናል ብለዋል፡፡

የዛላ ወረዳ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽ/ቤት የምግብ ዋስትና ባለሙያና የፕሮጀክቱ ተጠሪ አቶ ተመስገን ጨሬ በበኩላቸው በመኸር 2 ዓይነት የቦለቄ ዝርያዎች ቀርበው በ4 ቀበሌያት 40 አርሶ አደሮች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ መሆኑንና በ0.125 ሄክታር መሬት 1.5 ኩንታል ምርት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ በጓሮ አትክልት ረገድም ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው የጓሮ አትክልት ዝርያዎቹ በስፋት ቢቀርቡ ለወጣቱ የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት