በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ እና የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጆች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዳ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር በማዘጋጀት ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ፣ ለኢንተርን ሐኪሞችና ለአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች እያሰራጩ መሆናቸውን ገለፁ፡፡ኮሌጆቹ ምርቱን በብዛት በማምረት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጭምር የማዳረስ ዕቅድ እንዳላቸውም ገልፀዋል፡፡

በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የባዮ-ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ አቶ አዲሱ ፈቃዱ እንደገለፁት የንጽህና መጠበቂያው የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው የአሠራር መመሪያ መሠረት የተዘጋጀ ሲሆን ምርቱም በዋናነት አልኮል፣ ግሊሲሮልና ሃይድሮጅን ፔርኦክሳይድ የተባሉ ንጥረ-ነገሮችን በመጠቀም የሚዘጋጅ ነው ብለዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

ከዚህም ባሻገር በዩኒቨርሲቲው የኮሮና ቫይረስ ስርጭን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ-ኃይል ኮሚቴ አባላት የሆኑ በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንዲሁም ለአካባቢው ነዋሪዎች በተለያዩ መንገዶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑንም ገልጿል፡፡

የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺይፍ ኤክስክዩቲቨ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ በሽታ መግባቱ እንደታወቀ መጋቢት 7/2012 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከተቋቋመው ግበረ-ኃይል ባሻገር ንዑሳን ኮሚቴዎች በኮሌጅ ደረጃ በሽታውን የመከላከልና እንዲሁም የህክምና ሥራዎችን የሚሠራ ግብረ-ኃይል መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት በኮሌጁ የተቋቋመው ንዑስ ግብረ-ኃይል በዩኒቨርሲቲው፣ በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታልና በአካባቢው በሽታውን ከመከላከል ረገድ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልፀዋል፡፡

በኮሌጁ የፋርማሲ ት/ክፍል መምህርና የኮሌጁ ግብረ-ኃይል ፀሐፊ መ/ር አክሊሉ አየለ በበኩላቸው ግብረ-ኃይሉ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ዘዴዎች ስለበሽታው መከላከያ መንገዶች፣ ባህርያትና መሰል ጉዳዮች ግንዛቤ ሲፈጥር መቆየቱ፣ ከአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ጋር በመሆን ወደ ሆስፒታሉ የሚገቡ ግለሰቦችን በ ‘FEVER CLINIC’ የሙቀት መለኪያ ምርመራ እያደረገ መሆኑ፣ ወደ አርባ ምንጭ ማረሚያ ተቋም ጠያቂዎች እንዳይገቡና ታራሚዎች ለህክምና ወደ ውጪ እንዳይወጡ በማድረግ የኮሌጁ ሐኪሞች ታማሚዎቹ አገልግሎቱን ባሉበት እንዲያገኙ መደረጉ፣ ሳኒታይዘር በማዘጋጀት ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ፣ ለኢንተርን ሐኪሞች እንዲሁም ለአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች የማዳረስ ሥራ እየሠራ መሆኑ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኮሌጁ የማኅበረሰብ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ወይንእሸት ገ/ፃዲቅ በበኩላቸው ከዚህ በኋላ ግብረ-ኃይሉ ትኩረቱን የአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ አድርጎ እንደሚሠራ ገልፀው ከዞንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እስከ ወረዳ ጭምር በመውረድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በቂ ግብዓት የሚገኝ ከሆነ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርን በብዛት በማምረት ለአካባቢው ማኅበረሰብም ጭምር የማዳረስ ዕቅድ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

ግበረ-ኃይሉ አሁን ላይ ከሳይኒታይዘር ዝግጅትና ስርጭት ባሻገር የፊት ማስኮችን፣ መሸፈኛዎችን (ሺልዶችን) እና ሌሎች በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ የህክምና ቁሳቁሶችን የዓለም ጤና ድርጅት መለኪያዎችን ባሟላ መልኩ በቀላሉ ከሚገኙ ቁሳቁሶች በማዘጋጀት ለአገልግሎት እንዲውሉ ለአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ሐኪሞች አስረክቧል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት