የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ከጋሞ ዞንና ከአርባ ምንጭ ከተማ አመራሮች ጋር በመሆን በ2011 ዓ/ም ‹‹በአረንጓዴ አሻራ ቀን›› የተተከሉ ችግኞች ያሉበትን ሁኔታ እንዲሁም የዘንድሮው ክረምት የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አስመልክቶ እየተደረጉ ያሉ የቅድመ ዝግጀት ሥራዎችን በቤሬ ተራራና በተለያዩ ችግኝ ጣቢያዎች በመገኘት ዛሬ ግንቦት 15/2012 ዓ/ም ጎብኝተዋል፡፡


የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ ለተፋሰስና አካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስታውሰው የዛሬው ጉብኝትም አምና ‹‹በአረንጓዴ አሻራ ቀን›› የተተከሉ ችግኞች ያሉበትን ሁኔታ በመገምገም ለቀጣይ ሥራዎች አቅጣጫ መስቀመጥን እንዲሁም ዘንድሮ ለሚደረገው አገራዊ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር እየተከናወኑ የሚገኙ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለመፈተሽ ታስቦ ጉብኝቱ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡Click her to see the pictures

በቤሬ ተራራ ላይ አምና የተተከሉ ችግኞች የመፅደቅ ምጣኔ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ዳምጠው ዘንድሮም ዩኒቨርሲቲው ከአምናው በተሻለ ሁኔታ በርካታ ችግኞችን ለመትከል ብሎም ለመንከባከብ በርካታ የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎችን በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው በ2011 በጀት ዓመት ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ሥፍራዎች ከ22 ሺህ በላይ ችግኞች ማስተከሉን ገልፀው ከነዚህም መካከል በተወሰደ ናሙና 94 በመቶው መጽደቃቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ተክሉ ገለፃ ችግኞቹ በዚህ ልክ በከፍተኛ መጠን እንዲፀድቁ ዘንድሮ የነበረው የዝናብ ሁኔታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረጉን ገልፀዋል። ከዚህም ባሻገር ዩኒቨርሲቲው በርካታ ጥበቃዎችንና ተንከባካቢዎችን በመቅጠር ማሰማራቱ እንዲሁም የተለያዩ የሥነ-ሕይወትና ሥነ- አካላዊ ሥራዎች መሠራታቸው ለስኬቱ ከፍተኛ ሚና ነበራቸውም ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ዘንድሮም ለሚደረገው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ከአምናው በተሻለ ሁኔታ በ8ቱ የዩኒቨርሲቲው ችግኝ ጣቢያዎች የተለያየ ዝርያ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከጉብኝቱ በኋላ በተካሄደው አጠቃላይ ውይይት እንደተገለፀው ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ እየሠራ ያለው ሥራ አበረታች ስለሆነ ሊሰፋና ሊቀጥል ይገባል። በተጨማሪም ችግኞችን የመንከባከብ ሥራ፣ ምን ዓይነት ችግኝ በምን ዓይነት ቦታ መተከል ይኖርበታል እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ሥራው የዘርፉን ምሁራን በተሻለ ሁኔታ አሳትፎ እንዲከናወን ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ጊዜያት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት