ዩኒቨርሲቲው የ2012 ዓ/ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን አስመልክቶ ለ2ኛ ጊዜ የፊታችን ሰኞ ሰኔ 8/2012 ዓ/ም ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ የችግኝ ተከላ እንደሚያካሂድ ታውቋል፡፡ የችግኝ ተከላው በቤሬ ተራራ፣ በዩኒቨርሲቲው ስድስቱም ካምፓሶችና በመምህራን መኖሪያ አከባቢዎች ይፈፀማል፡፡Click here to see the pictures


ከዚህም ባሻገር የዚህ ክረምት የበጎ ፈቃድ አካል ሆኖ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ አስተባባሪነት ረቡዕ ሰኔ 10/2012 ዓ/ም በሁሉም ካምፓሶች የደም ልገሳ መርሃ-ግብር የሚካሄድ ሲሆን ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖችም የʻʻማዕድ ማጋራትʼʼ ሥራዎችንም በስፋት ለማከናወን እየተሠራ ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው በዚህ ክረምት 50 ሺህ ችግኞችን ለመትከል አቅዶ አየሠራ ሲሆን ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ መላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ራሱን ከኮሮናቫይረስ እየጠበቀ በሚዘጋጁ የተከላ መርሃ-ግብሮች ሁሉ በንቃት በመሳተፍ አሻራውን እንዲያሳርፍ ዩኒቨርሲቲው በአፅንዖት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ውድ ተማሪዎቹ በያሉበት አከባቢ ሁሉ ራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ እየጠበቁ ከማኅበረሰቡ ጋር አሻራቸውን በማኖር አረንጓዴና ውብ አገር እንድትኖረንና አረንጓዴ ኢኮኖሚ እንዲገነባ የበኮላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ጥሪውን እያስተላለፈ የቆይታ ጊዜውም የሠላምና የጤና እንዲሆንላቸው መልካም ምኞቱን ይገልፃል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የዘንደሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን የዓለም አከባቢ ቀንን ምክንያት በማድረግ ግንቦት 28/2012 ዓ/ም በይፋ ʻʻኮቪድ-19 እና አከባቢʼʼ በሚል መሪ ቃል ያስጀመረ ሲሆን በዕለቱም ከ2 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት