ዩኒቨርሲቲው በምርምር የተገኘውን እንሰትን በዘመናዊ መንገድ ጥራቱን ጠብቆ ከ10 ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለምግብነት ለማዘጋጀት የሚያስችል እርሾ በማምረት ለእንሰት አምራች አርሶ አደሮች ለሙከራ እያከፋፈለ መሆኑ ተገለፀ፡፡Click here to see the pictures


ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ባዮ-ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባባር የእንሰት ምርት ሂደትን በቴክኖሎጂና በፈጠራ ማገዝ የሚያስችል አዲስ ፕሮጀክት ይፋ ያደረገ ሲሆን ፕሮጀክቱ በዋናነት የእንሰት መፋቂያ ማሽኖችን አምርቶ ለአርሶ አደሩ ማዳረስ፣ የቆጮ ምርትን ለማብላላት ሲባል በጉድጓድ የመቅበር ሂደትን በማስቀረት ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ሂደቱን ለማፈጠን የሚረዳ እርሾ አዘጋጅቶ ለአርሶ አደሩ ማከፋፈልና ሌሎችንም ተያያዥ ጉዳዮችን ዓላማ አድርጎ እየሠራ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ  ዶ/ር  አዲሱ ፈቃዱ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር አዲሱ በእንሰት ምርት አዘገጃጀት ሂደት እንሰቱን ወደ ምግብነት ለመቀየር የሚደረገው የማብላላት (Fermentation) ሂደት ዋነኛው መሆኑን ጠቁመው ሂደቱ ከሁለት እስከ ሦስት ወራት ይፈጃል ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር አዲሱ በምርምር የተገኘውና እየተመረተ ለተጠቃሚ አርሶ አደሮች እየተከፋፈለ የሚገኘው እርሾ የምርት ሂደቱን በማሳጠር በ10 ቀናት ወስጥ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማግኘት እንደሚያስችል በተደጋጋሚ የላቦራቶሪ ሙከራ በመረጋገጡ በዩኒቨርሲቲው ላቦራቶሪዎች  ተመርቶ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች እየተሰጠ ውጤቱ በተግባር እየተፈተሸ ነው፡፡
እንሰት በባህላዊ መንገድ ተዘጋጅቶ ለምግብነት የሚውለው እንሰቱ ተፍቆና በጉድጓድ ውስጥ ቀብሮ  ለወራት በማቆየት ሲሆን በዚህ ጊዜም ከአፈር ጋር በሚኖረው ንክኪ ምርቱ በተለያዩ ባክቴሪያዎች ተጠቅቶ መጥፎ ጠረን እንደሚያመጣና በምግብነት ደረጃም ተፈጥሯዊ ጣዕሙን ከማጣቱ ባሻገር ጥራቱ ዝቅተኛ እንደሚሆን ዶ/ር አዲሱ ገልፀዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የአውሮፓ አገሮችና ቻይና ጥቅል ጎመንን ለማብላላት የሚጠቀሙበትን ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በመቀየር ለቆጮ ማብላያና ማስቀመጫነት በማዋል በዘመናዊ መንገድ ቆጮን ለማምረት የተደረገው ሙከራ አመርቂ ውጤት በማሳየቱ ቴክኖሎጂውን ከውጪ በማስመጣት እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታ በአከባቢው ከሚገኙ ቁሳቁሶች በማዘጋጀት ለአርሶ አደሩ እየተከፋፈለ ነው ብለዋል፡፡
የመፋቂያ ማሽን ማምረት እንዲቻል ሦስት ንድፎች ተዘጋጅተው በዘርፉ ባለሙያዎችና ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ተተችተው ማስተካከያ ተደርጎ ለምርት ሂደት ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር አዲሱ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች ባለመሟላታቸው  ማፋቂያ ማሽኑን ማምረት ያልተጀመረ ሲሆን አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት አምርቶ ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሦስት የሙከራ ጣቢያዎችን በዶርዜ፣ በግርጫና በአርባ ምንጭ መስርቶ እየሠራ ሲሆን በቀጣይም የቴክኖሎጂዎቹን ውጤታማነት እየፈተሸ በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ለሚገኙ እንሰት አብቃይ አርሶ አደሮች ለማዳረስ አቅዶ እየሠራ ነው፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት