ወድ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሁሉም ደረጃዎች ተማሪዎች በያላችሁበት ሰላምታችን ይድረሳችሁ!
ራሳችሁንና ሌሎችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል እያደረጋችሁት ያለው ጥንቃቄ ምን ይመስላል? በአሁኑ ወቅት ለመላው የዓለም ማኅበረሰብ ከባድ ፈተና የሆነውን የኮቪድ-19 ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል እያንዳንዳችን ከህዝባችንና ከመንግሥት ጋር ተባብረን ከሠራን ፈጣሪ ያሻግረናል፡፡ ስለሆነም ሳትዘናጉ ሁልጊዜ ጥንቃቄ አድርጉ፤ ሌሎችንም ደግፉ፡፡
ከወረርሽኙ ራሳችሁን እየጠበቃችሁ በእያንዳንዱ ቀን ራሳችሁን ከትምህርት ዓለም ጋር ማገናኘትን አትዘንጉ፡፡

አንድ ሰው በደረሰበት የትምህርት ደረጃ ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ በግሉ የሚያነብ ከሆነ ሁልጊዜ የትም ሆኖ ባልተቋረጠ ሁኔታ የራሱን ዕውቀትና ክሂሎት ማሳደግ እንደሚቻል ይታመናል፡፡ በመሆኑም በእያንዳንዱ ቀን ምን ያህል እንዳነበባችሁ በየቀኑ መጨረሻ ውሏችሁን እየገመገማችሁ እንድትኖሩ ያለኝን ምክረ-ሃሳብ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡
በአገራችን 2ኛውን ዙር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ፕሮግራም መሠረት በማድረግ በ6ቱም ግቢዎችና በአካባቢው ከግንቦት 28/2012 ዓ/ም ጀምሮ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች 50 ሺህ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ይህንን ስንፈጽም እናንተ ተማሪዎቻችን አብራችሁን እንዳለችሁ እያሰብን ነው፡፡ እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ልማት ዘመቻ ውጤቱ የተማራችሁበት ግቢ በትምህርት ላይ እያላችሁም ሆነ ከምረቃችሁ በኋላ አዕምሯችሁን የሚያስደስት ተፈጥሮ እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሊያደርግ እንደሚችል ይገመታል፡፡
ውድ ተማሪዎቻችን በያላችሁበት ከቤተሰብ እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን ችግኝ በመትከል በአገራችን የ2012 ዓ/ም አረንጓዴ አሻራ ማኖር እንዳትረሱ እጠይቃለሁ፡፡ በተጨማሪም ከቤተሰብ ሁሉም ማኅበረሰብ ራሱን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲጠብቅ የበኩላችሁን የማስገንዘብና መሰል ተግባራትን ከማድረግ እንዳትቆጠቡ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በራሴ ስም አደራ እላችኋለሁ፡፡
ፈጣሪ ሕዝባችንንና አገራችንን ከዚህ ፈታኝ ሁኔታ ጠብቆ እንዲያሻግረን ከልብ እየተመኘሁ የሁሉም ደረጃዎች ተማሪዎች ወደ ትምህርት ተቋማት ተመልሰው በተሟላ ሁኔታ የሚማሩበት ቀን እንዲሁም ሕይወት በአጠቃላይ ከስጋት ውጭ ሆኖ በተለመደው ሁኔታ እንድንኖር ፈጣሪ እንዲረዳን ሁላችንም በጸሎት እንበርታ እላለሁ፡፡
ለቀጣይ ትውልድ አረንጓዴና የበለፀገች አገር ለማስረከብ እንሥራ!
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት