በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር ውጤትን መሠረት በማድረግ በዘመናዊና ሳይንሳዊ መንገድ የተመጣጠነ የእንስሳት መኖ አዘገጃጀትና ለረጅም ጊዜ መኖን አቆይቶ መጠቀም ዙሪያ ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ከሚገኙ 6 ቀበሌያት ለተወጣጡ ሞዴል አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ


ሥልጠናው በአይዩሲ (IUC) ፕሮግራም በቤልጂየሙ ኬዩ ሊዩቨን (KU LEUVEN) ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት የመ/ር አሸናፊ አዛገ የምርምር ውጤትን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን ሥልጠናው በተመራማሪውና በተመራማሪው የሀገር ውስጥ አማካሪ በሆኑት ዶ/ር ይስሓቅ ከቸሮ ተሰጥቷል፡፡
የምርምር ሥራው አማካሪና የዘርፉ ምሁር የሆኑት ዶ/ር ይስሐቅ እንዳሉት የእንስሳትን የወተትና የሥጋ ምርት ከፍ ለማድረግ ልክ እንደ ሰው እንስሳትም የተመጣጠነ ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመው በተለይ በደረቅ ወቅት የሚከሰተውን የእንስሳት ምግብ ዕጥረት ከመቅረፍና ሳይንሳዊ መፍትሔዎችን ከማበጀት አኳያ የምርምር ሥራው ጉልህ ሚና ያበረክታል፡፡ ለአርሶ አደሮቹና ባለሙያዎቹ የተሰጠው ሥልጠና የምርምር ሥራዎችና አዳዲስ ሳይንሳዊ ቴክኖሎጂዎች ከወረቀት ባሻገር ተግባራዊ ተደርገው አርሶ አደሩ እንዲጠቀማቸው ለማድረግ ያለመ ሲሆን መሰል ሥልጠናዎችም ቀጣይነት የሚኖራቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ በእንስሳት ት/ክፍል የሥነ-ምግብ መምህርና በቤልጂየሙ ኬዩ ሊዩቨን ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት መ/ር አሸናፊ አዛገ የምርምር ሥራቸው በዋናነት በእንስሳት መኖ አዘገጃጀትና ለረጅም ጊዜ በማቆየት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልፀው አርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ የአየር ንብረቶች ወስጥ ሆኖ ለእንስሳቱ የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብና ማዘጋጀት የሚችልበትን ሁኔታ ማስቻልን ዓላማ አድርገው መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡
በክረምት ወይም በዝናብ ወራት ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት መኖ ብክነት መኖሩን በአንፃሩ ደግሞ በበጋ ወይም ደረቅ ወራት በከፍተኛ ሁኔታ የምግብ ዕጥረት እንዳለ የሚናገሩት ተመራማሪው ይህንን በክረምትና ዝናብ ወቅቶች የሚባክነውን መኖ በሳይንሳዊ መንገድ ማስቀረትና ሳይበላሽ አቆይቶ በበጋው ወይም በድርቅ ጊዜ መጠቀም ማስቻል የጥናታቸው ትኩረት ነው ብለዋል፡፡
እንደ መ/ር አሸናፊ ገለፃ የምርምር ሥራው የተከናወነባቸው አከባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የሙዝና የበቆሎ አምራች ሲሆኑ በብዛት የሙዝ ግንድና እና የበቆሎ አገዳ ተበላሽቶ ጥቅም ላይ ሳይውል ይባክናል፡፡ እነዚህን ሁለት ተረፈ ምርቶች ፈጭቶ አንድ ላይ በመደባለቅ አየር በማያስገባ መልኩ በጉድጓድ ወስጥ ልክ እንሰትን ለማብላለት እንደሚደረገው ከ3-12 ወር ቀብሮ በማኖር አርሶ አደሩ በድርቅ ጊዜ መጠቀም እንደሚችልና በዚህም በበጋ ወራት የሚገጠመውን የእንስሳት መኖ ዕጥረት በመቅረፍ ምርትና ምርታማነትን ከፍ ማድረግ እንደሚቻል በተደጋጋሚ የቤተ-ሙከራ ፍተሻ ተረጋግጧል፡፡ የምርምር ሥራው በመስክ ላይ እየተሞከረ መሆኑንም መ/ር አሸናፊ የጠቆሙ ሲሆን  የተሰጠው ሥልጠናም የሙከራው አካል ነው ብለዋል ፡፡
ከሠልጣኞች መካከል ከሼሌ ሜላ ቀበሌ የመጡት አርሶ አደር አዝማች ዓባይነህ አከባቢያቸው በብዛት በቆሎና ሙዝ አምራች መሆኑን ገልፀው በብዛት ከእነዚህ ምርቶች የሚገኙ ተረፈ ምርቶች ቶሎ የሚበላሹ በመሆናቸው የሚጣሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በሥልጠናው እነዚህን ተረፈ ምርቶች ለረጅም ጊዜ አቆይተን ለእንስሳት መኖ ማዋል እንደሚቻል ሥልጠናው ግንዛቤ ስለፈጠረልኝ ወደ ተግባር በመቀየር እጠቀማለሁ ብለዋል፡፡
በቆላ ሼሌ ቀበሌ የእንስሳት ግብርና ባለሙያ ወ/ሮ ነፃነት ግርማ በበኩላቸው እንደተናገሩት የእንስሳት መኖ አዘጋጀጀቱ ከዚህ ቀደም ከምናውቀው የተለየ ሲሆን በተለይ ግኝቱ በበጋ ጊዜ አርሶ አደሩ የሚገጥመውን የመኖ ዕጥረት የሚቀርፍ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ለአጠቃቀምና ለአዘገጃጀት ቀላል በመሆኑ አርሶ አደሮች ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንሠራለን ብለዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት