አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለ5 ዓመታት ሲያስተዳድረው የቆየውን የደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከልን ለጂንካ ዩኒቨርሲቲ ሰኔ 12/2012 ዓ/ም በይፋ አስረክቧል፡፡Click here to see the pictures

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሁለቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንቶችና ም/ፕሬዝደንቶች፣ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ አባል የሆኑት ዶ/ር የቻለ ከበደ፣ የማዕከሉ የአሁንና የቀድሞ እንዲሁም የሌሎች ዘርፎች ዳይሬክተሮችና የማዕከሉ ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡
የርክክብ ሥነ-ሥርዓቱን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ ያስጀመሩት የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ምርምር ማዕከሉን ከተረከበ ጊዜ አንስቶ ማዕከሉ የምርምር ማዕከል አቋም እንዲይዝ በርካታ ተግባራት በማከናወኑ ማዕከሉ በተሻለ ቁመና ላይ ይገኛል፡፡ ማዕከሉ አሁን ላይ ወደ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ መዛወሩ ከኢኮኖሚ አንፃር አዋጭ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ስምዖን ለጂንካ ዩኒቨርሲቲም ተጨማሪ እሴት የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡


የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የምርምር ማዕከሉን በ2008 ዓ/ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መረከቡን አስታውሰው ዩኒቨርሲቲው ማዕከሉን በአደረጃጀትና በመዋቅር ከማደራጀት ጀምሮ የሰው ኃይልና የተለያዩ አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንዲሟሉ በማድረግ ተቋሙ ለተቋቋመበት ዓላማ እንዲውል ዩኒቨርሲቲው በትኩረት ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል፡፡ ማዕከሉ ወደ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በመዛወሩ ደስታ እንደሚሰማቸው የተናገሩት ፕሬዝደንቱ ጂንካ ዩኒቨርሲቲም ማዕከሉን ወደ ተሻለ ቦታ ያሸጋግረዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልፀዋል፡፡
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ አባል የሆኑት ዶ/ር የቻለ ከበደ ሶሲዮሎጂና ሶሺያል አንትሮፖሎጂ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል ለመሆን የሚሠራበት መስክ መሆኑን ተናግረው ከዚህም አንፃር ዩኒቨርሲቲው የምርምር ማዕከሉን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መረከቡ ተገቢና ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡ ማዕከሉን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በቅንጅት ተባብረው ሊሠሩም ይገባል ብለዋል፡፡
የዛሬዋ ቀን በሕይወቴ ከማልረሳቸው ልዩ ቀናት መካከል አንዱ ነው ያሉት የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ፐሮፌሰር ገብሬ ኢንቲሶ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጥያቄያችንን ተቀብሎ ማዕከሉን ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር ሲተዳደር የነበሩበትን ችግሮች በመቅረፍና ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ አሳድጎና አደራጅቶ ስላስረከበን ዩኒቨርሲቲውን ከልብ እናመሠግናለን ብለዋል፡፡ የምርምር ማዕከሉ አሁን ላይ ወደ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ዞረ ማለት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን አይመለከተውም ማለት እንዳልሆነ የተናገሩት ፕሬዝደንቱ ምንም እንኳን የአስተዳደር ሥረውን ዩኒቨርሲቲያቸው ቢሠራም ማዕከሉን ግን የምንጠቀመው በጋራ ይሆናል ብለዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከልን በዳይሬክተርነት ከመሩ 4 የአ/ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህራን መካከል አቶ እሸቱ እውነቱ እና አቶ ስለሺ መንግሥቱ እንደተናገሩት ማዕከሉን መምራት መቻላቸው ትልቅ ዕድልና አጋጣሚ መሆኑን እንዲሁም በርካታ ልምዶችን ያገኙበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉን ዩኒቨርሲቲው ከተረከበበት ጊዜ አንስቶ ማዕከሉ በቁሳቁስ ከማደራጀት፣ የሰው ኃይል ከማሟላትና ከማብቃት፣ በማዕከሉ ወስጥ የሚገኘው ሙዚዬም ሁሉንም ብሄሮች ወካይ በሆነ መንገድ እንዲደራጅ ከማድረግ አንፃር የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም የርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው የምስክር ወረቀትና የባሕላዊ አልባሳት ስጦታ ለአ/ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ፣ ለአ/ም/ዩ አካዳሚክ ጉ/ም/ ፕሬዝደንትና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ አባል ዶ/ር የቻለ ከበደና ለምርምርና ማ/አገ/ም/ ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ የተበረከተ ሲሆን ማዕከሉን በዳይሬክተርነት ለመሩት አቶ ዮሐንስ ይትባረክ፣ አቶ እሸቱ እውነቱ፣ አቶ ተመቸኝ ጉቱና አቶ ስለሺ መንግሥቱ ምስጋና ቀርቧል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት