ከአምዩ ፕሬዝደንት ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነባር መደበኛ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የተላለፈ መልዕክት

ሁላችሁም እንደምን ቆያችሁ ? ፈጣሪ ባለንበት ሁሉ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ይጠብቀን፡፡ ከኮቪድ ወረርሽኝ ጥንቃቄ እያደረግን የወረርሽኙ ሁኔታ ሲቀንስ ወይም ሲቆም በቀጣይ የትምህርት ሂደት እንዴት ይደረጋል በሚለዉ ዙሪያ በሀገር ደረጃ ከተያዘዉ አቅጣጫ አንጻር ዝግጅት ላይ ትኩረት እንዲታደርጉ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

በመጀመሪያ ሁሉም ተማሪ የኮርስ ማቴሪያል በማግኘት ከትምህርት ይዘት ሳይርቅ ቆይቷል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በዚህ መሠረት በ2012 ትምህርት ዘመን በ2ኛዉ ሴሚስቴር ተጀምሮ የተቋረጠዉን የሴሚስቴር ትምህርት እስከ 2 ወር ጊዜ በማጠናቀቅ የ2013 ትምህርት ለመቀጠል ታቅዷል፡፡ በዚህ ሂደት ከወረርሽኙ አንጻር በጥንቃቄ ለማስኬድ እንዲረዳ በመጀመሪያ ተመራቂ ተማሪዎች ብቻ ወደ ዩኒቨርሲቲዉ ይመጣሉ፡፡ እነሱ ሲያጠናቅቁ ቀጥሎ ተመራቂ ያልሆኑ ተማሪዎች ይገባሉ፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ርዝማኔ (2 ወር) የ2012 ቀሪ ትምህርት እንዲጠናቀቅ ተደርጎ የ2013 ትምህርት ይቀጥላል፡፡ በዚህ መልኩ በመስራት ዉጤታማ ሆነን ያጋጠመዉን ፈታኝ ሁኔታ ለመሻገር እናንተ ተማሪዎች ባላችሁበት ሁሉ ወደ ዩኒቨርሲቲዉ እስከምትገቡ ድረስ በትኩረት እያነበባችሁ መቆየት ትልቅ አስተዋጽዖ ስለሚኖረዉ ቆይታችሁን የኮርስ ማቴሪያል በማንበብ ላይ እንዲታደርጉና ከራሳችሁ ትምህርት ክፍል ሃላፊ ጋር በየጊዜዉ ሃሳብ እንዲትለዋወጡ አደራ ለማለት እንወዳለን፡፡ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና መምህራን ከላይ በተጠቀዉ ሁኔታ የ2012 ቀሪ ትምህርትና የ2013 ትምህርት ለማስቀጠል አስፈላጊዉን ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል፣ በማድረግ ላይም ይገኛሉ፡፡

ከሁሉም በላይ ፈጣሪ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ፈታኝ ቫይረስ ወረርሽን ጠብቆ ያሻግረን!! ራሳችንና ሌሎችን ለመጠበቅ አንዘናጋ፡፡ ፈጣሪ ይርዳን፡፡